የአውሮፓ ፓርላማ 16 አባላት በጋዜጠኛና የኢንተርኔት አምደኛው እስክንድር ነጋ የተራዘመ እሥር የተሰማቸውን ብርቱ ሥጋት በመግለፅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
የደብዳቤውን ይዘት እና የተፃፈበትን ምክንያት አስመልክቶ የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ሃይንላይን “ፍሪደም ናው” የሚባለውን ተቀማጭነቱ ዋሽንግተን ዲሲ የሆነ በነፃነትና በፖለቲካ እሥረኞች ጉዳዮች ላይ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የፕሮግራም ጠበቃ ፓትሪክ ግሪፊትዝን አነጋግሯል፡፡
“የአቶ እስክንድር መታሠር በዓለምአቀፍ ደረጃ ጥበቃ የሚደረግለትን ሃሣቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱን የተጋፋ ነው፡፡ ደብዳቤውን የፃፉት የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጠየቁት እስክንድር ነጋ ሳይዘገይ እና ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ሥልጣናቸው የሚፈቅድላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ነው፡፡“ ብለዋል ፓትሪክ ግሪፊትዝ፡፡
“ግልፅነት ይጎድለዋል” እየተባለ በሚተቸው ፀረ-ሽብር ሕግ የተከሰሰው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ18 ዓመት እሥራት ተፈርዶበት ወህኒ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ከዓመት በፊት ታስሮ ለሁለት ወራት ያህል ከጠበቆች ጋር እንዳይገናኝ ተደርጎ መቆየቱን የሚያስታውሰው ዛሬ የወጣው የ“ፍሪደም ናው” መግለጫ እስክንድር የታሠረውና ተከስሦም የተፈረደበት የዐረቡን ዓለም አብዮት ዓይነት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ውስጥም ሊከሰት እንደሚችል የሚናገር ፅሁፍ በኢንተርኔት በማውጣቱና በግልፅም በመናገሩ እንደነበረ ጠቁሟል፡፡
ደብዳቤው የኢትዮጵያ መንግሥት ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የማክበር ግዴታ እንዳለበት ያስታውስና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ወደፊት እንዲመሩና ከመንግሥታት ማኅበረሰብ ቤተሰብነት ያቀላቅሏት ዘንድ የተለየ ዕድልና አጋጣሚ ያላቸው መሆኑን ያሣስባል፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡