የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የመዘዋወር መብት ገድቧል” በሚል ተከሠሠ

Your browser doesn’t support HTML5

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ “አድሏዊ አሠራር ተከትሏል” በሚል ክሥ ቀረበበት፡፡ አየር መንገዱ በበኩሉ፣ የፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሌለ ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከትግራይ ክልል ተነሥተው ወደ ዐዲስ አበባ የሚጓዙ የትግራይ ተወላጆችን የመዘዋወር መብት ገድቧል፤ ሲል፣ “ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች” የተሰኘ ድርጅት፣ ለፌደራሉ ከፍተኛ

ፍርድ ቤት ክሥ አቀረበ። ድርጅቱ በአቀረበው የክሥ ዝርዝር ላይ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ በፕሪቶርያው ስምምነት ከቆመ በኋላ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ መቐለ በረራ መጀመሩን አውስቷል፡፡ ኾኖም፣ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በተላለፈ የኢሜይል መልዕክት፣ በአየር መንገዱ በረራ ላይ ገደብ መጣሉን ያመለክታል። በዚኽም፣ አየር መንገዱ ከመቐለ ወደ ዐዲስ አበባ እና ከሽረ ወደ ዐዲስ አበባ የሚጓዙትን ሰዎች መብት መጣሱን ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ ክሡን ተቃውሞ በጹሑፍ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ “ተከሣሽ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ማንኛውም ተቋም፣ ለአገልግሎቱ መክፈል ለሚችሉ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ያቀርባል እንጂ፣ ከሣሽ እንደሚሉት፣ በትውልድ ቦታ ወይም ማንነት ላይ ተመሥርቶ ልዩነት አያደርግም፤” ብሏል፡፡

ከዚኽም በተጨማሪ፣ ድርጅቱ ባቀረበው የክሥ ዝርዝር ላይ፣ አየር መንገዱ፥ “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤” የሚለውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 32ን ተላልፏል የሚል ክሥ ተጠቅሷል። አካሔዱ፣ የትግራይ ተወላጆችን በእኩልነት የመገልገል ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ እንደኾነ፣ የድርጅቱ የሕግ አማካሪ አቶ መብርሂ ብርሃነ ገልጸው፣ ኹኔታው፥ ተጓዦችን ለእንግልት ከመዳረጉም ባሻገር፣ ለሕገ ወጥ አሠራር በር መክፈቱን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ ባቀረበው የክሥ መቃወሚያ፣ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 60 ዓመት የኾኑ የትግራይ ተወላጆችን ትኬት እንዳይቆርጡ ክልከላ ለማስተላለፍ፣ በሕግ የተሰጠው መንግሥታዊ ሥልጣን እንደሌለው ገልጿል፤ የተባለውንም ክልከላ “አላደረግኹም” ብሏል፡፡

አየር መንገዱ፣ በማቋቋሚያ ደንቡ ከተሰጠው አገልግሎት ውጪ፣ በሕግ ለሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተሰጡትን፣ የቁጥጥር ወይም የሕግ ማስከበር ሥራዎች እንደማያከናውንና የተባለው “የዕድሜ ገደብ ክልከላ”ም ተከሣሽን እንደማይመለከት አስገንዝቧል፡፡

አሁን ላይ፣ እንደ ማንኛውም የሀገር ውስጥ በረራ፣ ከመቐለ ወደ ዐዲስ አበባ ወይም ከሽረ ወደ ዐዲስ አበባ፣ ያለምንም ልዩነት በረራዎች እየተደረጉ በመኾናቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክሡን ዘግቶ እንዲያሰናብተው አየር መንገዱ በክሥ መቃወሚያው ጠይቋል፡፡