Your browser doesn’t support HTML5
የየመን መንግሥት የግንቦት ሰባትን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ ሰጥቷል ሲል ግንቦት ሰባት አስታውቋል፡፡
ግንቦት ሰባት በዌብ ሳይቱ ላይ ባሠፈረው መግለጫ “የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቶ መቆየቱ ማስታወቃችን ይታወሳል።” ብሏል፡፡
ግንቦት ሰባት ይቀጥልና “የየመን መንግሥት በህገወጥ መንገድ ያገተብንን የንቅናቄዓችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም - ይልና - የአገሩን የረዥም ጊዜ ጥቅም ማየት የተሳነው የየመን መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይልቅ አምባገኑን ወያኔ መርጦ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል።” ብሏል፡፡ “በዚህም ሳቢያ - ይላል የግንቦት ሰባት መግለጫ - የየመን መንግሥት ይቅርታ የማያሰጥ፤ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወዳጅ ጎረቤት ትሁትና ቀና ቢሆንም ጥቃት በሚያደርስበት የቅርብም ሆነ የሩቅ ጎረቤት ላይ ግን ቁጣውን የሚመጥን የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ያውቅበታል።”
ግንቦት ሰባት ያወጣውን ሙሉውን መግለጫ ለማየት ከሥር የተያያዘውን ማገናኛ ተጭነው ይከተሉ፡፡
http://www.ginbot7.org/2014/07/04/የመን-አቶ-አንዳርጋቸው-ጽጌን-ለወያኔ-ፋሽ/
ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የግንቦት ሰባት ቃል አቀባይ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የእንግሊዝ የውጭና የጋራ ብልፅግናው መሥሪያ ቤት ለንደን የሚገኙትን የየመን አምባሣደር ትናንት፣ ሐሙስ፣ ሰኔ 26/2006 ዓ.ም ጠርቶ እንዳነጋገራቸውና አምባሣደሩም አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጡ መሆኑን መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ባለሥልጣናትም እዚያው ለሚገኙት የአቶ አንዳርጋቸው ቤተሰቦች ይህንኑ ማሳወቁን አቶ ኤፍሬም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግን ዛሬ ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው እንዲሰጡት አለመጠየቁንና እንዳልተሰጡትም፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም አቶ አንድአርጋቸው መያዛቸውን ከሚሰሙ በስተቀር የየመን መንግሥትም ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለውም “… ይሁን እንጂ የመጠየቁ ጉዳይ ግምት ውስጥ ሊገባ ይችላል፤ አንዳርጋቸው የሽብር ቡድን የሚመራ ሽብርተኛ ነው፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ተከስሶ የተፈረደበት ወንጀለኛ ነው…” ብለዋል፡፡
ለዝርዝሩና ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡