አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች

አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ

ኃይለማርያም ደሣለኝ አሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ግንባሩ በአንድ ድምፅ የወሰነ በመሆኑ ተከታዩ የሃገሪቱ መሪም እርሣቸው እንደሚሆኑ ነው የሚታመነው፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች




የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ ለሁለት ቀናት ካካሄደው ጉባዔው በኋላ ያለፉ የረዥም ጊዜ መሪውን መለስ ዜናዊን የሚተካ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበሩን መርጦ ተበትኗል፡፡

የመንግሥቱ ቃል አቀባይ በረከት ስምዖን በሰጡት መግለጫ ኃይለማርያም ደሣለኝ የተመረጡት ከሦስት ዕጩዎች ነው፡፡

አቶ በረከት ስምዖን፤ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር



“በፓርቲያችን አጠቃላይ ግንዛቤ እና ስምምነት ወይም ውሣኔ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የሚመረጡት ሰዎች ለሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ፓርቲው በቀጥታ የሚያቀርባቸው የሚያቀርባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አቶ ኃይለማርያምም፣ አቶ ደመቀም ፓርቲውን ይወክላሉ፤ ፓርላማው እንዲያፀድቃቸውም ይቀርባሉ፡፡” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

ሊቀመንበሩ ኃይለማርያም ደሣለኝ እና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጭተው በፓርቲው የሚቀርቡት ከአንድ መቀመጫ በስተቀር ሙሉውን ኢሕአዴግ ለሚቆጣጠረው የተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ከደቡብ ኢትዮጵያ የወጡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑ ሲሆን ይህ ሹመት ወደሥልጣኑ አዲስ ትውልድ እየወጣ ለመሆኑ ማሣያ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በረከት በሰጡት መግለጫ “አመራሩ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ላልነበሩ፤ ነገር ግን ኃላፊነቱ በነፃ አውጭው ንቅናቄ ውስጥ ከተሣተፉት ለአዲስ ትውልድ መተላለፍ እንዳለበት ኢሕአዴግ ወስኗል፡፡” ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በውኃ ቴክኖሎጂ ምኅንድስናና በሥርዓተ ትምህርት ዓለም የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከመሾማቸው በፊት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ነበሩ፤ በማኅበራዊ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነውም ሠርተዋል፡፡

አቶ መለስ ምንነቱ ባልተነገረ ሕመም ምክንያት ማረፋቸው በተነገረ በሁለተኛው ቀን አቶ ኃይለማርያም ቃለመሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኀዘኑ ምክንያት በሚል መሠረዙ ይታወሣል፡፡

ፓርላማው የአቶ ኃይለማርያምንና የአቶ ደመቀን ሹመት ያፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ከክረምቱ ዝግ በኋላ ሥራ በሚጀምርበት በመጀመሪያው ዕለት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡