ባለፈው ዕሁድ የተካሄደው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ምርጫ እንዲሠረዝ ተጠየቀ

በእሥር ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ቅሬታ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ቅሬታ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት የፍርድ ቤት ውሎ



ጉዳያቸው በስምንት የተለያዩ ዶሴዎች የተያዘው ሃያ አምስቱ እሥረኞች ሁሉም ዛሬ ከሰዓት በኋላ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መቅረባቸውን የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ገልፀዋል፡፡
በአቶ ተማም መግለጫ መሠረት ፖሊስ የተጨማሪ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን ቀኑን አሣጥሮ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን አቶ ተማም አባቡልጉ አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የፍርድ ቤቱን ውሎ ለመከታተል ወደዚያው ሄደው የነበሩ ሌሎች ታዛቢዎች በአካባቢው እንዳንገኝ ተደርገናል ሲሉ አማርረዋል፡፡
ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ እንዳሉት ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ እንዲቀርብ ጉዳዩ ለጥቅምት 14/2005 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው ዕሁድ የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ሂደቱ እንዲታገድላቸው ክሥ አስገብተው የነበረ ቢሆንም በዳኞች አለመገኘት ምክንያት ማዘዣ በወቅቱ ሣይወጣላቸው መቅረቱን አቶ ተማም አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ “የእሥልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱና የኡለማና ፈትዋ ምክር ቤቱም ምርጫውን ለማካሄድ ሕጋዊነት የሌላቸው ናቸው፤ የኡለማና ፈትዋ ምክር ቤቱ ገለልተኛ አይደለም” ሲሉ የሚወቅሱት ጠበቃው አቶ ተማም የምርጫው ውጤት እንዲሠረዝላቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አስገብተው ለዓርብ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም መቀጠራቸውን ገልፀዋል፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡