በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን በሚገኘው የባቲ የጤና ጣቢያ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ የሆነችው ዘቢባ ሰይድ መድሃኒቶችን ከመድሃኒት ቤት ለመውሰድ መጥታለች። መድሃኒት ቤቱ ተጨናንቋል።
ከኦሮሚያ ዞንና ከቅርበቱ አንጻር ከአፋር ክልል የሚመጡ ተገልጋዮች በጤና ጣቢያው ይገኛሉ። ይሄንን መሰል የጤና ጣቢያ በተለይ በገጠር አካባቢ ማግኘት አይቻልም።
ለዚህ ነው የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ምንስቴር የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ያሰማራው።
እንደ ዘቢባ መሰል ከ32ሽህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በመላው ኢትዮጵያ ከወረዳ እስከ ጎጥ ድረስ ከማህበረሰቡ ጋር እየኖሩ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል፤ አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት በመስጠትና ከአቅማቸው በላይ የሆኑትን ጉዳዮች ወደ ክሊኒኮች፣ ጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች መላክ ነው ስራቸው።
ይሄ ስልት የተዋጣለት እንደሆነ በባራክ ኦባማ አስተዳድር በጤና ጉዳዮች የዋይት ሃውስ የበጀት አማካሪ ዶክተር ዝክየል ኢማኑዌል የተናገሩት።
“እዚህ በአግባቡ እየሰሩና ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ነገሮችን አስተውያለሁ። በተለያዩ የጤና ኬላዎች ብዙ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ተመልክቻለሁ። ይሄ በእውነቱ በኢትዮጵያ ከሚታዩ ትልቅ እመርታዎች አንዱ ነው። ውጤታማ ነው። ሀገሪቱ 32 ሽህ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን በአጭር ጊዜ አሰልጥና ወደ ገጠር ቀበሌዎች በመላክ የሚደነቅ ስራን ሲሰሩ ተመልክተናል። ማህበረሰቡን ያስተምራሉ፣ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትም ይሰጣሉ። የወባ በሽትን በመከላከል ረገድና የቤተሰብ ምጣኔን በተመለከተ የተሰሩ ስራዎች በእጅጉ የሚደነቁ ናቸው” ብለዋል።
ዶክተር ዚክ ኢማኑዌል በጎበኟቸው የአመያና ዎንጭ ወረዳዎች ከአንደ አመት በፊት የወባ መከላከያ አጎበሮች ተከፋፍለው ነበር፣ የወባ በሽታ መለላከልና ህክምና አገልግሎትም በዚሁ አመት ተስፋፍቷል። ውጤቱ በወባ በሽታ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር በ90 ከመቶ ቀንሷል፤ ከሁለት አይነት የወባ ተውሳኮች ማለት ከቫይቫክስና ፋልሲፋረም የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።
“በግልጽ እንደሚታየው የአልጋ አጎበሮች ስርጭት፣ የማህበረሰቡ ግንዛቤ መጨመር፣ መድሃኒት መርጨት፣ ፈጣን የምርመራ አገልግሎቶች መስፋፋት ለተገኘው ውጤት ተጠቃሽ ናቸው። አስቀድሞ በሽታው ከታወቀና የመከላከያ መንገዶች ካሉ፤ የወባ በሽታን መቀነስ ይቻላል” ሲሉ ዶክተር ኢማኑዌል ተናግረዋል።
ሌላኛው በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የተገኘው ለውጥ የወሊድ መቆጣጠርና የእናቶችና ህጻናት በእርግዝና ጊዜ፣ በወሊድና፣ ከወሊድ በኋላ የሚኖር የጤና ክትትል ነው።
ይሄንን ስራ ነው የኦባማ አስተዳድር የጤና አማካሪ የሆኑት ዶክተር ዚክ ኢማኑየል ያወደሱት።
“በጣም የሚያስመሰግንና የሚያኮራ ነው። ይሄ የሚያሳየው የተሟላ መርሃ ግብር ተቀርጾ በስራ ላይ ከዋለ የሚያስገርም ለውጥ እደሚያመጣ ነው።”
ዶክተር ኢማኑዌል ይህንን ይበሉ እንጂ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራት ዙሪያ የሚያሳስቧቸው ነገሮች እንዳሉ ሳይጠቁሙ አላለፉም። ከጤና ጥበቃ ምኒስትር ዶ.ር. ቴድሮስ አድሃኖም ጋርም በተገናኙበት ወቅትም ይህንንኑ ማሳባቸውን ገልጸዋል።
“በሳምንቱ መጀመሪያ ከሚኒስትሩ ጋር ስንገናኝ ያለምንም ገደብ የማይሰራውንና ሊሻሻል የሚገባ የምለውን እንድነግራቸው አበረታተውኝ ነበር” ይላሉ የቀድሞው የዋይት ሀውስ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ራም ኢማኑዌል ወንድም ዚክ ኢማኑዌል ።
“ያም ሆኖ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ከፍተኛ እንቅፋቶች ተጋርጠውበታል። የመጀመሪያው መሰረተ-ልማት ነው። ይሄንን ስል የጤና መሰረቶች=ማለት የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች እንዲሁም ዶክተሮችና ነርሶች ብዛት ሳይሆን፤ ሌሎችንም ያካትታል። መንገዶች፣ የውሃ የመብራትና የመሳሰሉት አገልግሎቶች አለመኖር አሁንም ከፍተኛ ችግር ነው።”
ከዚህም በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ የመከላከልና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የጤና ዘርፉ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ የጥራት ችግሮች ይታዩበታል ሲሉ ዚክ ኢማኑዌል ተናግረዋል።
ዶክተሮች፣ የጤና መኮንኖችና ነርሶች ቁጥር መጨመር እንዳለበትና ፤ ሀገር ለቀው በሚሄዱ ልምድ ባላቸው ሃኪሞች እግር ሌሎችን ለመተካት የተሻሉ ባለሙያዎችን ማሰልጠን እደሚሻ ተናግረዋል። ለሁሉም የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
“በዚች አገር ከፍተኛ መዋእለ-ንዋይ እያፈሰስን ነው። በየአመቱ ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዶላር ለጤና እንሰጣለን። ይች አገር ቁልፍ አጋር ነች። ብዙዎቻችሁ አንደምታውቁት ባለፈው አመት ፕሬዝደንት ኦባማ የግሎባል ሄልዝ ኢኒሺየቲቭን መስርተዋል። የዚህ መርሃ-ግብር አንዱ አሰራር በጤና ዙሪያ ከፍተና ለውጥ ያመጣሉ ብለን ያሰብናቸውን ጥቂት አገሮች እንድንመርጥ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ መርሃ ግብር ከተመረጡት ጥቂት አግሮች አንዷ ናት። ተጨማሪ ገንዘብና የቴክኒክ እገዛም ለማድረግ ተዘጋጅተናል። በዚህም ጠንካራ እመርታዎችን ለማግኘትና የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል ከመንግስቱ ጋር አብረን እንሰራለን።”
በጤና አገልግሎቱ ዙሪያ በወባ በሽታ፣ በኤች አይ ቪ ኤድስ፤ በእናቶችና ህጻናት ጤና ጥበቃ ዙሪያ የመረጃ ማሰባሰብ ስራዎች አሁን ካሉበት ዝቅተኛ ደረጃ እንዲሻሻሉም ዚክ ኢማኑዌል አሳስበዋል።