የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ሥርዐት ብቻ ተፈጻሚ እንዲኾን የተላለፈው ውሳኔ፣ ከዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት አንድ ቀን፣ 2015 ዓ.ም. አንሥቶ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ኾኗል፡፡ በአዳማ ከተማም፣ የነዳጅ ዲጂታል ግብይቱን የማስጀመርያ ሥነ ሥርዐት ተከናውኗል።
የዲጂታል ግብይቱ የኔትዎርክ ችግር ሊገጥመው ስለሚችል፣ እክሉ እስኪሻሻል ድረስ፣ የገንዘብ ኖት ክፍያ ለተወሰነ ጊዜ አማራጭ መኾኑ እንዲቀጥል፣ የነዳጅ ተጠቃሚዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ፣ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ሥርዐቱን ለማቀላጠፍ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ይናገራል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ 16 ቀን፣ በዐዲስ አበባ የተጀመረው ዲጂታል የነዳጅ ግብይት፣ ከዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት አንድ ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በብሔራዊ ደረጃ ተፈጻሚ ኾኗል። በዚኽም መሠረት፣ በዛሬው ዕለት በአዳማ በተከናወነው ዲጂታል የነዳጅ ክፍያ ማስጀመርያ መርሐ ግብር ላይ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ይህንኑ ሥርዐት ያቀላጥፋል ያለውን አሠራር ማለትም ሲቢኢ ብርን ይፋ አድርጓል።
የኔትወርክ እክልን የሚጠቅሱ ተጠቃሚዎች ግን፣ አሁንም የዲጂታል ክፍያ ሥርዐቱ ላይ ስሞታ ያሰማሉ።
ምሕረቱ ግርማ፣ የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪ ሲኾን፤ “ናፍጣ ልቀዳ፣ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ነበር እዚኽ የደረስኹት፡፡ አሁን ከረፋዱ 5 ሰዓት ኾኗል፡፡ የክፍያ መንገዱ ጊዜያችንን እየወሰደ ነው። የተጠቃሚው መብት ተጠብቆ እንደቀድሞው በብር እየከፈለ ቢቀዳ ጥሩ ነበር፡፡” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
አያይዞም “አሁን ከኢትዮጵያ ውጭ የመጣ ሰው፣ እንዴት ነው የሚቀዳው? በመኾኑም፣ አሠራሩ እስኪስተካከል ድረስ፣ የብር ኖት ክፍያ በትይዩ ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ እኔ እንደ ዕቅዴ በዚኽ ሰዓት ዐዲስ አበባ መድረስ ነበረብኝ፡፡ የመኪናው ባለቤትም ነጋዴውም አውቄ የቆየኹ ነው የሚመስላቸው።” ብሏል።
የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ሹፌር ብንያም በላይ ፤ “ዲጅታል የክፍያ ሥርዐት መጀመሩ ወይም አለመጀመሩ ለእኛ ያለው ጥቅም ምንድን ነው? ምክንያቱም፣ እኛ ማደያ ላይ ቤንዚን አግኝተን አናውቅም፡፡ ቤንዚን
ቢመጣም በወር አንድ ቀን ነው፡፡ እርሱንም ቢኾን ተሰልፈን አናገኘውም፤ ብንቀዳም ዲጅታሉን የመጠቀም ዕድሉ የለንም።” ብሏል።
ቤንዚንን፣ በሊትር በናረ ሕገ ወጥ ዋጋ እንደሚገዛ የገለጸው ብንያም፣ “የዲጅታል ክፍያ ሥርዐቱ ለውጥ ያመጣ እንደኾነ የሚታይ ይኾናል፤” ሲል አስተያየቱን አካፍሏል።
አቶ አሕመድ ዒሳ፣ በአዳማ የኦይል ሊቢያ ሥራ አስኪያጅ እና ባለሀብት ሲኾኑ፤ “በቀን ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ይዘን ወደ ባንክ እንሔድ ነበረ፡፡ አሁን ወደ 1ነጥብ5 ሚሊዮን የሚኾነውን በቴሌ ብር ወደ ባንክ እንልካለን፤ ኔትዎርኩም ደኅና ነው፡፡ ያ ለሀገርም፣ ለእኛም ጥሩ ነበረ። አሁን ግን፣ በተወሰነ መልኩ ጫናው በዛ፤ አሁን ለምሳሌ፥ ቴሌ ብር ይሠራል፤ የባንኮቹ ኔትዎርክ ግን አይሠራም፤ ምናልባት ወደፊት፣ መንግሥት እና ባንኮቹ የኾነ መፍትሔ ያበጁ እንደኾነ አላውቅም።” ይላሉ።
“የግንዛቤ መፍጠር ሥራው፣ በባንኮቹም በኩል ክፍተት ይታይበታል፤” ያሉት አቶ አሕመድ፥ የቤንዚን እጥረትን በተመለከተ፣ ጥያቄው ለመንግሥት አቅርበው ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንደኾኑ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ፣ ለነዳጁ ዲጅታል የክፍያ ሥርዐት የሚበጅ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ መላን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ አድርጓል። የባንኩ የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ የኾኑ፣ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ፣ ከ1ነጥብ7 ትሪሊዮን በላይ ብር በሞባይል ባንኪንግ ዝውውር መፈጸሙን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የነዳጅ ግብይቱ በዲጅታል የክፍያ ሥርዐት እንደሚከናወን፣ በመንግሥት ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም፣ ሕዝቡ ከክፍያ ሥርዐቱ ጋራ እንዲለማመድ የማስተዋወቅ እና የውስጥ ዝግጅትም ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ “ከወር በፊት በዐዲስ አበባ ጀምረናል፡፡ ከእርሱም ልምድ ቀስመናል፡፡ አሁን ከዝግጅት አኳያ የሚቀረን ነገር የለም። ኾኖም አንዳንዴ የሚገጥመን ችግር ይኖራል፡፡ እርሱም፣ የኔትዎርክ እና የደንበኞቻችን አጠቃቀሙን አለማወቅ ስለኾነ፣ ይህን ተከታትለን መንገድ የምናስይዝ ይኾናል።” ብለዋል።
የአዳማ ከከተማ ንግድ ቢሮ ሓላፊ አቶ ጥሎ ዱግዳ፣ የነዳጅ እጥረት በከተማዋ መኖሩን ገልጸዋል። “በአዳማ የቤንዚን ግልጋሎቱ ለባጃጅ ብቻ አይደለም፡፡ ኢንዱስትሪዎች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎችም ለፍጆታ ይጠቀሙበታል። ስለዚህም እጥረት ይስተዋላል፤ ይህን ለክልሉም አሳውቀን መሻሻሎች ቢታዩም፣ አሁንም በመንግሥት በኩል ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።” ብለዋል።
መንግሥት የነዳጅ ብክነትንና ምዝበራን ለመቆጣጠር ሥራ ላይ ማዋሉን የገለጸው የዲጅታል የነዳጅ ግብይት ሥርዓት፣ ከዛሬ ግንቦት አንድ ቀን ጀምሮ፣ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ መዋሉ ታውቋል።