በፈጣን ሁኔታ እያበበ ባለው የኤርትራ የማዕድን ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስሱ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የጥንቃቄ እርምጃ ካልወሰዱ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ውስጥ ተሣታፊ የመሆን አደጋ እንደሚጠብቃቸው ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውቋል፡፡ በማዕድን ልማት ሥራው ላይ የተሠማራው የውጭ ኩባንያ “የግዳጅ ሥራ አይፈቀድም” ብሏል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
በፈጣን ሁኔታ እያበበ ባለው የኤርትራ የማዕድን ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስሱ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የጥንቃቄ እርምጃ ካልወሰዱ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ውስጥ ተሣታፊ የመሆን አደጋ እንደሚጠብቃቸው ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውቋል፡፡ በማዕድን ልማት ሥራው ላይ የተሠማራው የውጭ ኩባንያ “የግዳጅ ሥራ አይፈቀድም” ብሏል፡፡
ዋና ፅሕፈት ቤቱ ኒው ዮርክ - ዩናይትድ ስቴትስ የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው ትናንት ባወጣው መግለጫው ነው፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዋች ለመግለጫው መሠረት ያደረገው ዋና መሥሪያ ቤቱ ቫንኮቨር - ካናዳ የሆነው ኔቭሰን ሪሶርስስ የሚባለው ኩባንያ ኤርትራ ውስጥ ባለው የማዕድን ልማት ይዞታው ግንባታ ውስጥ በግዳጅ የተሠማሩ ሠራተኞች አለመሠማራታቸውን ሳያረጋግጥ መቅረቱ መሆኑን ገልጿል፡፡
“የግዳጅ ሥራ ስለመኖሩም ክስ ሲቀርብ ኩባንያው ለማስተባበል አለመቻሉም ሥጋቱንና የችግሩን አሣሣቢነት ያጎላዋል” ብሏል የመብቶች ተሟጋቹ ድርጅት፡፡
የኤርትራ መንግሥት እጅግ የተስፋፋ የግዳጅ ሥራና ብዝበዛ እንደሚያካሂድ የገለፀው “ክፉ ነገር አትስሙ፡- በኤርትራ የማዕኁን ዘርፍ ውስጥ የግዳጅ ሥራ እና የኩባንያዎች ኃላፊነት” ብሎ በሰየመው ባለ 29 ገፅ ሪፖርቱ “ኤርትራ ውስጥ የሚሠሩ የማዕድን ልማት ኩባንያዎች በዚያ የመንግሥት ብዝበዛ ውስጥ እጃቸውን የማስገባት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል” ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች አስጠንቅቋል፡፡
በኤርትራ ማዕድን ለማልማት የመጀመሪያው የሆነው ኔቭሰን ኩባንያ ለእነዚያ ሥጋቶች ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጥ መቅረቱንና በኋላም ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሱበትን ክሦች ለማስተናገድ ችግር ውስጥ መግባቱን ሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጿል፡፡
ኔቭሰን ሪሶርስስ ኩባንያ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ “ኔቭሰን በቢሻ ማዕድን ማውጫ ላይ የሚከናወኑት ሥራዎች ኃላፊነት በተመላው መንገድ እንደሚከናወኑ የማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለውና ይህም የሚደረገው የደኅንነት፣ የአስተዳደር እና የሰብዓዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን መሠረት አድርጎ መሆኑን የኩባንያው ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሊፍ ዴቪስ መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡
ኔቭሰን ስድሣ ከመቶ ድርሻውን የያዘው ቢሻ የማዕድን አክስዮን ማኅበር ወደ አንድ ሺህ ሠራተኞችን በቀጥታ መቅጠሩንና ደኅንነቱ የተጠበቀ ለሠራተኞቹ ድጋፍ የሚሰጥ የሥራ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ፕሬዚዳንቱና ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
ሠራተኞቹ ተገቢ በሆነ የቅጥር ሂደት እንደሚያልፉ፣ ከኩባንያው የሚያገኙትን ከሥልጠና እስከ ምግብና ነፃ ሕክምና ያሉ ጥቅማ ጥቅሞችንና አገልግሎቶችን መግለጫው ጠቅሶ “በቢሻ የምልመላ ሠራተኞችን መጠቀም አይፈቀድም” ሲል በጉልህና ደጋግሞ አስታውቋል፡፡
የኤርትራ መንግሥት በሂዩማን ራይትስ ዋች ስለቀረቡበት ክሦችና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ውንጀላዎች መልስ እንዲሰጥ ተጠይቆ ባለሥልጣናቱ መግለጫው የደረሣቸው ዛሬ መሆኑንና መልስም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እየተዘጋጀ መሆኑን የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ፅሕፈት ቤት ገልጿል፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ