በዐዲስ አበባ የንግድ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው አካል ጉዳተኞች አቤቱታ አሰሙ

Your browser doesn’t support HTML5

በዐዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች፣ ንግድ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው እና ንብረቶቻቸው የተወሰዱባቸው አካል ጉዳተኞች፣ ለችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡ አቤቱታቸውንም፣ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማስገባታቸውን አስታወቁ።

የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ፣ 160 አካል ጉዳተኞች፣ በከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች እንግልት እንደ ደረሰባቸው ጠቅሰው፣ አቤቱታቸውን ለኮሚሽኑ ማስገባታቸውን ተናግረዋል።

የአካል ጉዳተኞቹን አቤቱታ አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጥ የተጠየቀው የዐዲስ አበባ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ፣ “መረጃው አልደረሰኝም፤ የማውቀው ነገር የለም፤” ብሏል፡፡

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ አንዱ መኾኑን የገለጸውና “ሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ንግድ አክስዮን ማኅበር” ሰብሳቢ ኢዮብ ደስታ፣ በዐዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 8፣ ከረሜላ ፋብሪካ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የ181 አባላቱ የንግድ ቤቶች እንደነበሩ ጠቅሷል፡፡

ቦታው፣ በ2001 ዓ.ም. አካል ጉዳተኞቹ በጊዜያዊነት እንዲሠሩበት የተሰጣቸው እንደነበር ያወሳው ኢዮብ፣ ላለፉት 15 ዓመታት፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሲያስተዳድሩበት መኖራቸውን ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን፣ “ከሸራ የተሠሩ ንግድ ቤቶች ይፍረሱ” ተብሏል በሚል፣ የንግድ ቤቶቹ መፍረሳቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ቅሬታው የቀረበለት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከ160 በላይ የሚኾኑ አካል ጉዳተኞች በጽ/ቤቱ ተገኝተው፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታ እንዳቀረቡለት በመግለጫው አስታውቋል።

ስለ ጉዳዩ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት፣ በኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ፣ አካል ጉዳተኞቹ ልዩ ልዩ ቅሬታዎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

በጊዜያዊነት በተሰጣቸው ቦታ ላይ የከፈቷቸው የንግድ ቤቶች ከመፍረሳቸው በፊት፣ የከተማ አስተዳደሩ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን የጠቀሰችው ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ኢየሩሳሌም ግርማ ደግሞ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዳላገኘች ገልጻለች፡፡

ኢየሩሳሌም እንደተናገረችው፣ የንግድ ቤቶቹ ባለፈው ሳምንት ከፈረሱም በኋላ፣ አቤቱታ ለማሰማት ወደ ከተማ አስተዳደሩ ቢሔዱም ተገቢ ምላሽ አልተሰጣቸውም፤ ይልቁንም እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡

የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሚመለከተው፣ የዐዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ የሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ቀረበ ስለተባለው ቅሬታ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ፣ የቢሮው ምክትል ሐላፊ ወ/ሮ ገነት ቅጣው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ቤቶቻቸው በመፍረሳቸው ለችግር ተዳርገናል የሚሉት የአካል ጉዳተኞቹ፣ መንግሥት፣ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የአካል ጉዳተኞቹን አቤቱታ አስመልክቶ በአወጣው መግለጫ፣ የንግድ ቤቶችን የማፍረስ ሒደት፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን ሊከተል እንደሚገባው ገልጾ፣ በተለይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት እንዲከናወን አሳስቧል፡፡ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነሯም፣ የመንግሥት አካላት እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንዲያከብሩ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በአካል ጉዳተኞቹ የቀረቡትን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ የማጣራት ሥራ እንደሚያከናውንና ግኝቱንም ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ኮሚሽነር ርግበ አመልክተዋል፡፡ ከዐዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ምላሽ እንዳገኘን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡