በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ እንደኾነ መቀጠሉን ኢሰመኮ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በኢትዮጵያ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ኾኖ መቀጠሉን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ለመባባሱ ዋና ምክንያት ነው ያለው ትጥቃዊ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተባብሶ መቀጠሉንና እስከ አሁን ያሉበት የማይታወቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡

የኦሮሚያ እና የዐማራ ክልሎች ደግሞ፣ ከፍተኛ የመብቶች ጥሰት የሚፈጸምባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እንደኾኑ፣ ሪፖርቱን ያቀረቡት፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶር. ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ እየተሻሻለ እንደኾነ በመግለጽ፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከጣላቸው ገደቦች ውስጥ የተወሰኑትን ማንሣቱን፣ በቅርቡ አስታውቆ ነበር፡፡

ከዛሬው የኢሰመኮ ሪፖርት በኋላ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ አጭር ቆይታ ያደረጉት ዶር. ዳንኤል በዚኹ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ድምዳሜ፣ በኢትዮጵያ በመንግሥት የሚፈጸሙ ስልታዊ የመብቶች ጥሰት አዝማሚያዎች አለመኖራቸውን የሚያንጸባርቅ እንደኾነ ተናግረዋል።

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።