የዋሺንግተን ዲሲ መንግሥት በብርዱ ምክንያት መጠለያ አዘጋጀ

  • VOA

ፎቶ ፋይል

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 38 ከተሞች መጠለያ በሌላቸው ሰዎች ቁጥር ዋና ከተማይቱ ዋሺንግተን ዲሲና አካባቢዋ ቀዳሚ መሆናቸውን ዛሬ የወጣ ሪፖርት አስታውቋል፡፡

ከእያንዳንዱ 10ሺሕ ነዋሪዎች 124.2 የሚሆኑት በድህነትና በመጠለያ እጦት ሥር ይገኛሉ፡፡

የዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ መንግሥት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪው ቁጥር በ34.2 ከመቶ መጨመሩን አሳይቷል፡፡

በያዝነው የአየር ሁኔታ ወይም በረዷማ የክረምት ወቅት መጠለያ ለሌላቸው የአስቸኳይ ጊዜ መቆያ አዘጋጅቷል፡፡

በመሆኑም የዋሺንግተን ዲሲ አስተዳደር ዛሬ ባወጣው ማስታወቂያ እርዳታ የሚያስፈልገው መጠለያ የሌለው ሰው የሚያዩ ሰዎች ወይም እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች በተከፈተላቸው የቀጥታ (ሃትላይን) የስልክ አግልግሎት እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡

በዚህም መሠረት በዲሲ የክረምት ዕቅድ ሥር በተከፈቱት 202 399 7093 ወይም 211 ወይም 1-800-535-7252 ላይ እንዲደውሉ መክሯል፡፡

የሙቀቱ መጠን ከ32 ዲግሪስ ፋረንኸይት ወይም ከዜር ዲግሪ ሴልሽየስ በታች በወረደ ጊዜ ሁሉ መጠለያ የሌላቸው ሰዎች በሙሉ የመጠለያ አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡