ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ

Your browser doesn’t support HTML5

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት የሥልጣን ዘመናቸው ነሐሴ ላይ ሲያበቃ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ። ባሸሌት ይሄን ያሉት የመንግሥታት ድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ጉብዔ የ50ኛ ዙር ስብስባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ሲሆን፣ ለውሳኔያቸው ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዞችን ይዞታ በተመለከተ ያካሄዱትን ጥናት ለጉባኤው ያቀረቡት ባሸሌት በጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በግል ምክንያታቸው ጡረታ ለመውጣት መወሰናቸውን ገልፀዋል። ውሳኔያቸው ከቻይና ጉዞአቸው ጋር በተያያዘ ከቀረበባቸው ትችት ጋር እንደማይያያዝም አስታውቀዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ባሸሌት ወደ ቻይና ባደረጉት ጉዞ ቤይጂንግ በሺንጃንግ ግዛት በሚገኙ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ወደ 2 ሚሊየን ዊገሮችን በግዳጅ ማሰሯን ሳያወግዙ ቀርተዋል በሚል ትችት አቅርበውባቸዋል። ባቸሌት ለሚዲያ ባደረጉት ገልፃ፣ በድጋሚ በኃላፊነታቸው መቀጠል እንደማይፈልጉ ገልፀው መልቀቂያቸውን ለመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ያስገቡት ወደ ቻይና ከመጓዛቸው ከሁለት ወር በፊት መሆኑን አስረድተዋል።

"ዋና ፀሃፊው እንድቀጥል እንደሚፈልግ ነግሮኝ ነበር። ነገር ግን አስረዳሁት። በራሴ ምክንያት - ከዚህ በኋላ ወጣት ሴት አይደለሁም እናም ከረጅም እና ያካበተ የሥራ ልምድ በኃላ ወደ ሀገሬ፣ ወደ ቤተሰቦቼ መመለስ እፈልጋለሁ።” ያሉት ባሸሌት “ለረጅም ዓመታት በሚኒስትርነት፣ ፕሬዝዳንትነት እና ከፍተኛ ኮሚሽነርነት ካገለገልኩ በኋላ አሁን ግዜው ይመስለኛል። አሁን የምመለስበት ጊዜ ነው።" ብለዋል።

ቀደም ሲል ለጉባኤው አድርገውት በነበረው ንግግር የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች አንስተው አስተያየት ሰጥተው ነበር። ባሸሌት ከቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልፀው እነዚህም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት መንግሥት የሚጠቀምባቸውን ፖሊሲዎች፣ በብሔራቸው እና በኃይማኖታቸው ለሚገፉ ሰዎች ሊደረግ ስለሚገባው ጥበቃና ለሴቶች ሊሰጥ የሚገባ ሕጋዊ ከለላን እንደሚያጠቃልሉ ተናግረዋል።

ባሸሌት "በዊገሮች እና በሌሎች በሺን ጃንግ የሚገኙ በአብዛኛው ሙስሊም በሆኑ ሰዎች ላይ ስለሚደርሰው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አንስቻለሁ። በሞያ ትምህርት ማሰልጠኛ ማዕከል እና በሌሎች የእስር ቦታዎች ስለሚደርሰው የጅምላ እስር አካሄድ እና የመብት ጥሰትንም ጨምሮ። የኔ ቢሮ በሺን ጃንግ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚያዘጋጀው ግምገማ ያንን እንዲያካትት እየተደረገ ነው። ሪፖርቱ ከመታተሙ በፊት ለመንግሥት ተልኮ በመረጃው ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል።" ሲሉ በተተቹበት ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በባሸሌት ላይ ትችት ከሚያቀርቡት መካከል አንዱ መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገ “ለዊገሮች ዘመቻ” የተሰኘ ተቋም መስራችና ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሩሻን አባስ ናቸው። አባስ በቅርቡ 'ባሸሌት የቤይጂንግን ትርክት በማስተጋባት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ላይ አፊዘዋል' ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር። በትዊተር ገፃቸው ላይም የመንግሥታት ድርጅቱ የተመሰረተበትን መርሆ እና ኃላፊነታቸውን ዘንግተዋል በማለት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ጠይቆ ነበር።

የመብት አቀንቃኞች ባሸሌት ለረጅም ግዜ ሲጠበቅ የቆየውን በቻይና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የተዘጋጀውን ሪፖርት እንዲያወጡ ሲወተውቷቸውም ቆይተዋል። ከፍተኛ ኮምሺነሯም ሪፖርቱ እሳቸው ሥራቸውን ከመልቀቃቸው በፊት እንደሚወጣ ገልፀዋል።ቤይጂንግ ማንኛውንም የመብት ጥሰጥ ክስ አትቀበልም።

ከፍተኛ ኮሚሽነሯ ለጉባኤው ባቀረቡት ረዘም ያለ ረፖርት በዓለም ዙሪያ የተስፋፉ የመብት ጥሰቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንዳወደመ እና ለድህነት እንደዳረገ አስረድተዋል።

ባሸሌት ንግግራቸው በተለይ በዩክሬን እየተደረገ ባለው ጦርነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ጦርነቱ የብዙ ሰዎችን ህይወት ያጠፋ፣ ያበላሸ እና ያወደመ ነው ብለዋል። በተለይ በንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰው ስቃይ ለመጪው ትውልድም እጅግ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ መሆኑንም አስምረውበታል።

ባቸሌት በንግግራቸው በየካቲት 17 ቀን በዩክሬን ላይ ወረራ የፈፀመችውን ሩሲያ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጦርነቱ ተቃዎሚ ሰልፈኞችን በጅምላ ማሰሯን አውግዘዋል። በሩሲያ ገለልተኛ ሚዲያዎች ላይ እየጨምረ የሄደው ቅድመ ምርመራ እና ክልከላ እጅግ የሚያሳዝን ነው ሲሉም ኮንነዋል።