የካንኩን ጉባዔ

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባዔ በሜክሲኮዋ የመዝናኛ ከተማ ካንኩን ትናንት ተጀምሯል፡፡

ጉባዔው የሚነጋገረው የዓለምን ሙቀት የሚጨምሩ አፋኝ ጋዞችን ለመቀነስ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ተሰብባቢዎቹ የሚመክሩት ጋዞቹን ለመቀነስ የሚያስችሉ አጠቃላይ ገዥ ሕጎችን በማውጣት ላይ ሣይሆን በተናጠል የቀረቡ ጉዳዮች ወደፊት ሊራመዱ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ለመጭዎቹ ሁለት ሣምንታት በሚካሄደው በዚህ የካንኩን ጉባዔ ላይ የታደሙት ከ190 ሃገሮች የተላኩ መሪዎች፣ የመንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተጠሪዎችና ወኪሎች ናቸው፡፡

ስብሰባውን የከፈቱት የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ፊሊፕ ካልዴሮን ዓለም ቆፍጣና እርምጃዎችን ፈጥኖ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ካልዴሮን “የአየር ንብረት ለውጥ በሜክሲኮም ሆነ በዓለም ዙሪያ አሁን እያየነው ያለ አደጋ ነው” ብለዋል፡፡ እንደማሣያም በራሣቸው ሃገር በሜክሲኮ፣ በጎረቤታቸው በጓቲማላና በእሥያም በፓኪስታን በቅርብ ወራት የደረሱ ብዙ ሕይወት የጠየቁና ውድመት ያደረሱ የጎርፍ አደጋዎችን አንስተዋል፡፡ በአፍሪካና በሩሲያም የደረሱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎች የሰውን ልጅ ጤናማ ሕይወትና ኑሮ እያወኩ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ በአሁኑ አያያዙ ከቀጠለና የዓለማችን ግለት እያሻቀበ የሚሄድ ከሆነ የደሴት ሃገሮች ሕልውና አደጋ ላይ መሆኑም ተወስቷል፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡