የአማራ ክልል ልዩ ኅይል አዛዥ የቀድሞ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን እና መምሕርት መስከረም አበራ ከእስር ተለቀዋል

Your browser doesn’t support HTML5

ለ29 ቀናት በእስር የቆዩትና በአንድ ወቅት የአማራ ክልል ልዩ ኅይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር የነበሩት ቢሰጥ ጌታሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ዛሬ ከእስር መለቀቃቸውን ተናገሩ። በተመሳሳይ የ“ኢትዮ ንቃት” ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ ዛሬ ከእስር መለቀቋን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግራለች።

ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን ዛሬ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለ29 ቀናት በእስር መቆየታቸውንና የታሰሩበት ምክንያት ሳይነገራቸው፣ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የዞን አመራሮች ፊት ቀርበው “ይቅር ተብለሃል” በሚል ዛሬ ጠዋት 3:30 ላይ ያለ ዋስ መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

የቀድሞ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ "የታሰርኩበትን ምክንያት ማንም የነገረኝ የለም እሱን ወደፊት የማጣራው ይመስለኛል።የዞን አመራሮች ፊት ቀርቤያለሁ እነሱም ዋስ አያስፈልግም ይቅር ተብለሀል አሉኝ እናም ዛሬ እረፋዱ 3:30 ላይ ከእስር ለቀቁኝ " ብለዋል።

በአንድ ወቅት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት የብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ ምክትል የነበሩት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን በእስር በቆዩባቸው ቀናት ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልደረሰባቸው አክለው ገልፀዋል

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ“ኢትዮ ንቃት” ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ ዛሬ ከእስር ተለቃለች፡፡ የስር ፍርድ ቤት በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንድትፈታ የሰጠው ትዕዛዝ በትናንትናው ዕለት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጽናቱን ተከትሎ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢወስድም፣ ይግባኙ ውድቅ ተደርጎበት ከእስር ልትፈታ ችላለች።

አመሻሹ ላይ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ቆይታ ያደረገችው መስከረም ከቤተሰቦቿ ጋር በሰላም መቀላቀሏን ገልፃለች።

"የተለቀኩት አሁን ከ11: 30 አካባቢ ነው አዲስ አበባ ከሚገኙት ቤተሰቦቼ ጋር በሰላም ተገናኝቻለሁ ልጆቼ ያሉት ሀዋሳ ነው ነገ ልጆቼን አገኛቸዋለሁ " ብላናለች። በእስር በቆየችበት ጊዜም ምንም አካላዊ ጥቃት እንዳልደረሰባት መስከረም ተናግራለች።