ለሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩነት ውድድር ማይክ ፔንስ በቀጥታ በዶናልድ ትረምፕ ላይ አነጣጠሩ

Your browser doesn’t support HTML5

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ፣ የሪፐብሊካን ፓርቲውን ዕጩነት እንዳይቆናጠጡ ለመከላከል፣ በዚኽ ሳምንት፣ በርካታ ዕጩዎች ፉክክሩን ተቀላቅለዋል፡፡ ከዐዲሶቹ ተፎካካሪዎች መካከልም፣ የትረምፕ ታማኝ ምክትል ፕሬዚዳንታቸው የነበሩት ማይክ ፔንስ አንዱ ናቸው፡፡

የቪኦኤ የብሔራዊ ጉዳዮች ዋና ዘጋቢ ስቲቭ ሀርማን፣ ከኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት ባጠናቀረው ዘገባ፣ ይህን ለማድረግ ሲያመነቱ የከረሙት ፔንስ፣ በቀድሞ አለቃቸው ጠባይ ላይ ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ፣ ትላንት 64ኛ የልደት በዓላቸውን አክብረዋል፡፡ ለአራት ዓመታት በምክትልነት በአገለገሏቸው አለቃቸው ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ትችት የሰነዘሩት፣ በዚኹ የልደት በዓል አከባበር ላይ ነው፡፡

“እንደኔ ዕምነት ማንም ራሱን ከህገ መንግሥቱ በላይ አድርጎ የሚያይ ሰው ፈጽሞ ፕሬዚደንት ሊሆን አይገባም፡፡ ከህገ መንግሥቱ በላይ ካላደረጋችሁኝ የሚል ሰው ፈጽሞ ዳግመኛ ፕሬዚደንት መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡

እ.አ.አ. በ2021 ጥር ስድስት ቀን፣ በጊዜው ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ማይክ ፔንስ፣ ጆ ባይደን በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ማሸነፋቸውን የሚጸድቅበትን ምክር ቤታዊ ሒደት ለማደናቀፍ ፈቃደኛ አለመኾናቸውን ተከትሎ፣ የዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች፥ “ማይክ ፔንስ ይሰቀል! ማይክ ፔንስ ይሰቀል!” የሚል መፈክር እያሰሙ ምክር ቤቱን እንደወረሩ ይታወሳል፡፡

ማይክ ፔንስ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲያቸው፣ በታሪኩ የሚታወቅባቸውን የኢኮኖሚ እና የውጭ ፖሊሲ የሚከተሉ ሰው ናቸው፡፡

የፓርቲያቸው ዋና መሠረት በኾነው፣ የወንጌላዊ ክርስትና፣ የነጮቹ ዘርፍ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የኾኑት ፔንስ፣ ከፓርቲያቸው ዕጩ ተፎካካሪዎች ሁሉ፣ ፅንስ ማቋረጥን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ከሁሉም የበለጠ ወግ አጥባቂነታቸውን ለማሳየት ተነሣስተዋል፡፡

“በአሜሪካ ታሪክ ከነበሩት ፕሬዚዳንቶች ሁሉ፣ ጠንካራ ፀረ ፅንስ ማቋረጥ አቋም የነበረውን አስተዳደር መርተው ሲያበቁ፣ ዶናልድ ትረምፕም ኾኑ ሌሌቹ፣ ለፅንስ መከበር ከመቆም ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ናቸው፤” ብለዋል ፔንስ።

በጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ጄሬሚ ሜሰን በሰጡት አስተያየት፣ “የምክትል ፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ጎድቷቸዋል፡፡ እንዲያውም፣ በእርሳቸው ላይ የደረሰው፣ በየትኛውም ምክትል ፕሬዚዳንት ላይ አልደረሰም፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ የግላቸው ሎሌ ወይም አገልጋይ ይመስል፣ ከመጠን ያለፈ ታማኝነት ይጠብቁባቸው ነበር፤” ብለዋል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለው ከተሰናበቱ በኋላ፣ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ወደ ኋይት ሐውስ ለመመለስ የበቁ ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ አንዱ፣ እአአ በ1968 ሪቻርድ ኒክሰን ሲኾኑ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሦስት ዓመታት በፊት፣ ዶናልድ ትረምፕን አሸንፈው፣ ከምክትላቸው ከማይክ ፔንስ ጋራ ኋይት ሐውስን ያስለቀቋቸው፣ ጆ ባይደን ናቸው፡፡

የጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ጄሬሚ ሜሰን በሰጡት አስተያየት፣ ትረምፕ፥ ፓርቲውን ቀይረውታል፡፡ የእርሳቸውን ቦታ ለመውሰድ የሚፈልጉት፣ ሮን ደሳንቲስን የመሳሰሉትን ካያችኋቸው፣ ተቆርቋሪ ዐጣን፣ የሚለውን ብሶተኛ አጀንዳ አንግበው ደጋፊ ለመሰብሰብ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ በሊበራሎች እና ወግ አጥባቂዎች መካከል በሚካሔዱ ርእዮተ ዓለማዊ እሰጣ አገባዎችም ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ማይክ ፔንስም ቢኾኑ፣ በዚኽ መድረክ፣ ከፖሊሲ ይዞታ አኳያ በመከራከር መግባት የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡ እንግዲህ እርሳቸው የማይችሉት ወይም እስከ አሁን ያላየነው ነገር ቢኖር፣ የሕዝብ ብሶት ይዞ ማጯጯኹን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስናየው ደግሞ፣ ከትረምፕ በኋላ ሪፐብሊካን ፓርቲው የሚፈልገው እርሱን ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለማንኛውም፣ የቀጣዩ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ መረጣ ውጤት፣ ምንም ይኹን ምን፣ ማይክ ፔንስ፥ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ በአንድ ወቅት አብረዋቸው ተወዳድረው፣ በኋላም ምክትላቸው ኾነው ያገለገሏቸውን ፕሬዚዳንት ለመፎካከር የተነሡ፣ የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ኾነዋል፡፡