በደቡብ አፍሪካ፥ ተረፈ ምግብን መልሶ በመጠቀም ሜቴን ጋዝን የመቀነስ ጥረት

Your browser doesn’t support HTML5

የደቡብ አፍሪካ ንግድ ድርጅቶች እና ሌሎችም ተቋማት፣ ተረፈ ምግብን ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከመጣል ይልቅ፣ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል፣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሜቴን ጋዝ ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

በአንድ ተቋም የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው፣ ደቡብ አፍሪካ፥ በዓመት 10 ሚሊዮን ቶን ተረፈ ምግብ አላት፡፡ተረፈ ምግብ፣ በማከማቻ በርሜሉ ተጠራቅሞ በሚበሰብስበት ጊዜ፣ ሜቴን የተባለውን ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይለቃል። ሜቴን ጋዝ፣ አደገኛ ከሚባሉት የግሪን ሐውስ ጋዞች አንዱ ሲኾን፣ ከካርቦዳይኦክሳይድ በበለጠ፣ የዓለም ሙቀት እንዲጨምር አስተዋፅኦ ያደርጋል።

“ኧርዝ ፕሮቦቲክ” የተሰኘ የአገር ውስጥ ድርጅት፣ ተረፈ ምግብ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ መጣሉንና የሜቴን ጋዝ ወደ ከባቢ አየር መለቀቅን ለመቀነስ አንድ ዘዴ ቀይሷል። ይኸውም፣ ንግድ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ግለሰቦች፣ በወር 130 ዶላር እንዲከፍሉና ተረፈ ምግባቸውን መልሰው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ በማድረግ ላይ ነው።

ሒደቱ እንዲህ ነው፤ ድርጅቱ፣ ማጠራቀሚያ በርሜል እና “ቦካሺ” የተባለውን ዱቄት መሰል ነገር፣ ለደንበኞቹ ያቀርባል። “ቦካሺ”፣ ከስንዴ እና ሩዝ ገለባ፣ እንዲሁም ከዕንጨት ፍቅፋቂ የሚሠራ ሲኾን፣ ከረቂቅ ተሕዋስያን (ማይክሮ ኦርጋኒዝም) ጋራ ተቀላቅሎ ይቀርባል። ቦካሺ፣ ከተረፈ ምግብ ጋራ በሚቀላቀልበት ጊዜ፣ ወደ ብስባሽ ወይም ማዳበሪያ ከመቀየሩ በፊት፣ ቶሎ እንዲብላላና እንዲፈራርስ ያደርጋል። ይህም ሒደት፣ የሜቴን ጋዝ መፈጠርን ያስቀራል።

ቅዱስ አልባንስ የተባለው ኮሌጅ፣ ተረፈ ምግብን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን፣ እንደ ሌሎቹ የኮሌጁ ሥራዎች አድርጎ መንቀሳቀስ ጀምሯል። ከኮሌጁ ማዕድ ቤቶች የሚወጣውን ተረፈ ምግብ፣ ዝም ብሎ ከመወርወር ይልቅ፣ 100 በሚኾኑ ቦካሺ በርሜሎች አጠራቅመው፣ ወደ ማዳበሪያነት ይቀይሩታል።

የኮሌጁ የግቢ ሓላፊ ጃን ንኩና፣ ሥራው ለኮሌጁ አስፈላጊ እንደኾነና ወጣቶችን ማስተማር እንደሚገባ ተናግረዋል። ማዳበሪያው፣ ለኮሌጁ የአትክልት እና የአበባ ሥፍራ እንደሚውል፣ ጃን ንኩና ጨምረው ገልጸዋል።

የ“ኧርዝ ፕሮቦቲክ” ባለቤት ጋቪን ሄሮን እንዳሉት፣ በየወሩ 500 ቶን ተረፈ ምግብ፣ ከቆሻሻ መጣያው በመሰብሰብ፣ በማሽን ታግዞ ወደ ማዳበሪያ የሚቀየርበትን ሒደት ያፋጥናሉ።

“ዓለም በቀውስ ውስጥ ናት፡፡ ሁላችንም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዓለምን ችግር ላይ እንደጣላት እናውቃለን። ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን። በግልም ኾነ እንደ ድርጅት፣ በተፈጥሮ ከባቢያችን ላይ የምናደርሰውን ተጽእኖ ለመቀነስ መጣር አለብን፤” ብለዋል ጋቪን ሄሮን። ማዳበሪያው ለገበያ አይቀርብም። የአትክልት ሥፍራን ለሚከባከቡ ድርጅቶች እና ለግለሰቦች በነፃ ይሰጣል።