አማዞን ጫካ ውስጥ ለአርባ ቀናት ተሰውረው የቆዩ ህፃናት ተገኙ

Your browser doesn’t support HTML5

አዲስ የተለቀቀው ቪዲዮ አማዞን ድቅድቅ ደን ውስጥ ለ40 ቀናት ተሰውረው የቆዩ አራት እህትማማችና ወንድማማች ህፃናት የተገኙበትን ሁኔታ ያሳያል። ይህ የህፃናቱ ታሪክ የጀመረው ይጓዙበት የነበረው አይሮፕላን በገጠመው እክል ጥቅጥቅ ባለው የኮሎምቢያ ደን ውስጥ በመውደቁ ነው።

አር.ቲ.ቪ.ሲ. ኖቲሲያስ የሚባለው የመንግሥት ቴሌቪዥን ያወጣው ቪዲዮ ፓይለቱንና የልጆቹን እናት ጨምሮ ሦስት አዋቂዎች መሞታቸውን፤ አይሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ግን የገቡበት ሳይታወቅ የቆየ አራት ህፃናት በህይወት መገኘትና ከዚያም የአገሬው ጠባቂዎችና የኮሎምቢያ ጦር ህፃናቱን ሲመግቡ ያሳያል።

በዕድሜ አነስ ያሉቱ ህፃናት የተገኙት በኮሎምቢያ ካኬታ እና ጉዋቪየር ግዛቶች መካከል ነው።

እዚያው ደን ውስጥ እያለ አንደኛ ዓመቱን የያዘውን ህፃን ጨምሮ ትናንሾቹ ልጆች የተሰወሩት እነሱን ያሳፈረው ሴስና 206 አይሮፕላን ከወደቀበት ካለፈው ሚያዝያ 23 ጀምሮ ነበር።

አያታቸው ፊዴንሲዮ ቫለንሲያ ከህፃናቱ ጋር እንደገና የተገናኙበትን ቅፅበት እጅግ የተደሰቱባት መሆኗን ሲገልፁ “እነሆ አራቱን የልጅ ልጆቼን አየሁ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉም በህይወት አሉ። በጣም ደክሟቸዋል። ቢሆንም ጥሩ እንክብካቤ እሚያገኙበት ሆስፒታል ውስጥ ናቸው። ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን አውቃለሁ” ብለዋል።

የሠራዊቱ ጀኔራል ፔድሮ ሳንቼዝ ህጻናቱ መገኘታቸውን ለማብሰር ስለደረሳቸው ጥሪ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡

“እኔ የሠራዊቴ ድምጽ ነኝ፣ አደገኛ በሆነው የአማዞን ደን መካከል፣ 2ሺ566 ኬሎሜትሮችን አንድ በአንድ እያንዳንዷን እርምጃ በማሰስ የተጓዙት የአገሬው ሰዎች ድምጽ ነኝ፡፡” ያሉት ጀኔራሉ “ያ ከቦጎታ፣ ሊማ ከዚያ እስከ ፔሩ ድረስ በእግር የመጓዝ ያህል ነው፡፡ ልከ ከሰዓት በኋላ 11 ሰዐት ከሩብ ሲሆን፣ የልዩ ኃይሉ አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ጆን ኮቶአ፣ ሪፖርት አደረገልኝ “ተአምር! ተአምር! ተአምር!” ያ ለፍለጋው (ለኦፕሬሽኑ) የሰጠነው ቁልፍ ነው፡፡ “ በማለት ህጻናቱን ስለታደጉ ሰዎች ብርታትና ጥረት አስረድተዋል፡፡

“ኦፕሬሽን ሆፕ” ወይም “አሰሳ ተስፋ” በሚል ስም በተካሄደው ፍለጋ ቢያንስ 11 አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ከጦሩ ልዩ ኃይሎች መምሪያ ከ150 በላይ ወታደሮች፣ እንዲሁም ከአገሬውና የአካባቢው ሰዎች 73 ሰዎችና የቤልጅየም አዳኝ ውሾች ተሰማርተዋል፡፡

ህጻናቱ በህይወት እንዲቆዩ የረዳችው የ13 ዓመቷ ሌስሊ ናት፡፡ የሚያርፉበትን ቦታ በማመቻቸት፣ በተለይም ትንሹን ህጻን ወንድሟን በመንከባከብ ፣የሚያስፈልገውን የምግብ ዓይነት በማፈላለግ፣ እሷም እንዲሁ በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልጋትን ምግብ ለማግኘት በመጣጣር ሁሉንም ለማሰንበት የረዳች ናት፡፡

የኮሎምቢያ መከላከያ ሚኒስትር ኢቫን ቬላስኬዝ ከሌስሊ ጋር የተገናኙበትን ቅጽበት ሲገልጹ “ትልቋ ሴት ልጅ የደረሰቸው ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነበር፣ የልጆች ፕሮግራም ለማየት ቴሌቪዥኑ እንዲከፈት መጠየቅ የጀመረችው ወዲያኑ ነበር፡፡” ብለዋል፡፡ “ እኛ ስንደርስ በትክክል ከአልጋዋ ውስጥ ገብታ ቴሌቭዥን እየተመለከተች ነበር፡፡” ሲሉም አክለዋል ሚኒስትሩ፡፡

አራቱ ህጻናት በቦጋታ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ውስጥ እያገገሙ ነው፡፡ ሆስፒታል ሲደርሱ በውሃ ጥም ድርቀትና በጥቃቅን ነፍሳት ከመነደፋቸው በቀር ምንም ችግር የለባቸውም፣ እስካሁን ደህና ማገገም መያዛቸው ተነግሯል፡፡