ኢትዮጵያ - አሜሪካዊ የሚኔሶታው ባለሀብት ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ታስረው ተለቀቁ

Your browser doesn’t support HTML5

ዩናይትድ ስቴትስ ሚኔሶታ ክፍለ ግዛት ውስጥ በግል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ አቶ ተሺታ ቱፋ ባለፈው አርብ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውለው ትናንት መለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቪኦኤ ገለጹ። አቶ ተሺታ “ሜትሮፖሊታን ትራንስፖርቴሽን ኔትወርክ” የተባለ ኩባኒያ ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

የባለሃብቱን እስርና መለቀቅን በተመለከተ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት ወንድማቸው አቶ ትቤሶ ቱፋ፤ አቶ ተሺታ እናታቸውን ለማስታመም ከርሳቸው ቀደም ብለው ወደኢትዮጵያ ተጉዘው እንደነበረ ገልጸው ሁለቱም አርብ ዕለት ወደዩናይትድ ስቴትስ ለመመለስ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ከገቡ በኋላ አቶ ተሺታ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ወንድማቸው በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንደማያውቁ የተናገሩት አቶ ትቤሶ “ተለቀዋል” የሚለውን ዜና በተመለከተ "እኛ መፈታቱን የምናረጋግጠው ዩናይትድ ስቴትስ ምድር ሲገባ ነው"የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቪኦኤ ስለአቶ ተሺታ ቱፋ ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።