ከአዲስ አበባ 705 ኪሜ ወደ ኢትዮጵያ ኬንያ ድንበር ሞያሌ መንገድ ጸሃይ በርትታለች።
ክው ብለው በደረቁት የግራር ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ያለከልካይ የሚነፍሰው ንፋስ ደማቅ ብርቱካናማውን አፈር እንዳሻው ይገልጠዋል።
ድርቁ አካባቢውን አረንጓዴ ቀለም አይቶ የማያውቅ በረሃ አስመስሎታል።
ግራና ቀኝ በቀይ አፈር አጃቢነት ከተነጠፈው አስፋልት ቀለሙ በለቀቀ ጥቁርና ነጭ ቀለም 705 ኪሎሜትር የሚል የኮንክሪት አምድ ቆሟል።
ከአዲስ አበባ 705 ኪ.ሜ መሆኑን ከሚያሳየው ምልክት ስር አንዲት ደባራ ላም ወድቃለች። ከወደወገቧ ጥቁር ቡናማ ከወደ እግሮቿ ሳያር የተቆላ ቡና መሰል -- ደባራ ቀለም አላት።
መቼ እንደሞተች ባይታወቅም። ስጋዋ በጸሃይ ሃሩር ፈሳሹን አትንኖ ቆዳዋ ከአጽሟ ጋር ተጣብቋል። ሽታ የሚባል ነገር የለም። ቀድሞውንም ለሁለት አመት ያህል የዘለቀው ድርቅና የጸሃዩ ብርታት የሚሞቱትን ከብቶች በቀናት ውስጥ ያደርቃቸዋል።
ከብቶቻቸው የሚሞቱባቸው አርብቶ አደሮች ሳር ፍለጋ ከሞት የተረፉትን ለማዳን ስለሚገሰግሱ፤ ቆም ብሎ ቆዳ ለመግፈፍ ጊዜውን አንዳንዴ ደግሞ አቅሙ አይኖራቸውም።
705ኛው ኪሎሜትር በቦረና ዞን የሚታየውን ድርቅና ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሞት በግልጽ ያሳያል። ከ1.5 ኪሎሜትር እስከ 2 የሚሆን ርቀት ውስጥ 16 የሞቱ የከብት ቅሪቶችን ቆጥረናል። ይሄ እንግዲህ በመንገዱ ዳር ያየንው ብቻ ነው። ውስጣ ውስጡን ያለቀውን፣ ወድቆ የሚታየውን የእንስሳት ቅሪት አድማስ ይቁጠረው።
የሚበዛው ነዋሪ ከከብት እርባታ በሚገኙ ተዋጽዖዎች የሚተዳደርበት ቦረና ከ60-75 ከመቶ የሚሆኑ ከብቶች መሞታቸው ይገመታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ የሚያዝያው ወር የገና ዝናብ ለሁለተኛ ጊዜ ሳይጥል በመቅረቱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ከብቶች ሞተዋል።
“የእንስሳት ሞቱ በከብት ብቻ አልተወሰነም። ግመልም፣ ፍየልም የጋማ ከብቶችም ሞተዋል።” ይላሉ ሊበን አሬሮ የቦረና ዞን አርብቶ አደር ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ።
“በድርቁ ሳቢያ የሞቱትን ከብቶች ጠቅላላ ቁጥር ለማወቅ ጥረት ቢያዝም፤ እስካሁን ይሄን ያህል ለማለት የሚያስችል መረጃ አላሰባሰብንም።”
የሞቱት ከብቶችን ቁጥር የኢትዮጵያ መንግስት በቁጥር ማስቀመጥ ባይችልም። በአካባቢው ለተረጂነት የተጋለጡ ሰዎችን ቁጥር በአግባቡ ይገልጻል።
በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና በሴፍቲ ኔት ከሚረዱት ሰዎች በተጨማሪ ለእናቶችና ህጻናት፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለአረጋዊያን የሚሰጠው እርዳታ ሲጨመር ግማሽ የሚሆነው የቦረና ህዝብ እርዳታ እየተሰጠው ይኖራል።
ከ705ኛው ኪሜ ቀድሞ አልፎም እስከ ኬንያ ድንበር እንዲሁ የቀውስ ቀጠና ነው። ሰሜን ኬንያም ቢሆን በዚህ ድርቅ ክፉኛ ተጠቅቷል። በሳምንታት የዘገየው የሃገያ ዝናብ ካልጣለ፤ አካባቢው ወደከፋ የሰብዓዊ እልቂት እንዳያመራ ተሰግቷል።