የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር(UNHCR)፣ በግጭት ምክንያት ከላስአኖድ አካባቢ ተፈናቅለው በኢትዮጵያ እየኖሩ ያሉትን ሶማልያውያን ስደተኞችን ለመርዳት፣ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ስደተኞቹን ለመርዳት፣ 116 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ቢያስታውቅም፣ ከዚኽ ውስጥ የተገኘው ግን፣ ሁለት በመቶው ብቻ እንደኾነና ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው፣ ለአሜሪካ ድምፅ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በዚኽም ሳቢያ አብዛኞቹ ስደተኞች፣ ያለምንም መጠለያ፣ በሜዳ ላይ እና በዛፎች ሥር ተጠልለው ኑሯቸውን በመግፋት ላይ እንዳሉ ገልጿል፡፡
ስለ መግለጫው ማብራሪያ የሰጡት፣ የተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ጃብ ባልዴ፥ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እና የግል የርዳታ ተቋማት፣ ለዚኽ ችግር ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዲሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፣ ዩኤስ-ኤይድ፣ ለኢትዮጵያ ሲሰጠው የነበረውን ርዳታ በማቆሙ፣ በስደተኞች የርዳታ አቅርቦት ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ በሶማሊላንድ በተከሠተው ግጭት የተነሣ፣ ከላስአኖድ አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ ሶማልያውያን ስደተኞች፣ ሲያቀርበው የነበረው የነፍስ አድን ርዳታ፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መስተጓጎሉን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከዚኽ ቀደም፣ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የሚገኙትን ከ100ሺሕ በላይ የኾኑ ሶማልያውያን ስደተኞችን ለመርዳት፣ የ116 ሚሊዮን ዶላር የርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም፣ ከዚኽ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ የተገኘው፣ ኹለት ከመቶው ብቻ እንደኾነ አመልክቷል፡፡ በዚኽም ምክንያት፣ እያደገ ያለውን የስደተኞቹን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም፤ ብሏል፡፡
ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ከ100 ሺሕ በላይ ስደተኞች መካከል የተወሰኑት፣ ወደ አካባቢው ማኅበረሰብ እንደተጠጉና 20 ሺሕ ያህሉ ደግሞ በሶማሌ ክልል፣ ሚርቃን በተባለ መጠለያ ጣቢያ እየኖሩ እንዳሉ የተቋሙ መግለጫ አመልክቷል፡፡ ብዙዎች ደግሞ እንዲሁ ሜዳ ላይ ተበትነው እና በዛፍ ሥር ተጠልለው እየኖሩ በመኾናቸው፣ ለተለያዩ ጥቃቶች መጋለጣቸውን ገልጿል፡፡ ከመጠለያ እጥረት ባሻገርም፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው፣ የምግብ፣ የመጠጥ ውኃ እና የሕክምና አገልግሎት በቂ አይደለም፤ ይላል፡፡
በመግለጫው የተጠቀሱት፣ የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ጃብ ባልዴ፣ ለስደተኞቹ በእጅጉ አስፈላጊ የኾነውን የነፍስ አድን ርዳታ በማቅረብ በጊዜው መርዳት ካልተቻለ፣ አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ይህ ከመከሠቱ በፊት፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግም ተማፅነዋል፡፡
በስደተኞች ጉዳይ ላይ በሚመክር በአንድ የባለድርሻዎች መድረክ ላይ የተገኙት፣ የኢትዮጵያ ተወካዩ ማማዱ ጃብ ባልዴ፣ የርዳታ ጥሪው፣ ሁሉንም አካላት እንደሚያካትት፣ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ከላስአኖድ የተቀበለቻቸው ስደተኞች ወደ 100ሺሕ እንደሚደርሱ የጠቀሱት ተወካዩ፣ ስደተኞቹ ባረፉበት ቦታም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የክልሉ ሓላፊዎች፣ አስፈላጊውን ርዳታ እየሰጡ እንደኾኑ መመልከታቸውን አንሥተዋል፡፡ ይህም ድጋፍ ይቀጥል ዘንድ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡ ኾኖም፣ ስደተኞቹም ኾኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ በአግባቡ እየታገዙ ባለመኾኑ፣ በሳምንቱ፣ የርዳታ ተማፅኖ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ በመኾኑም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ለጋሽ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ እና የግል በጎ አድራጊዎች ጭምር፣ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው የስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት አኳያ፣ በአገሪቱ የአስቸኳይ የርዳታ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ያመለከተው የዩኤንኤችሲአር መግለጫ፣ አቅርቦቱ ግን በእጅጉ ውስን እንደኾነ ገልጿል፡፡
በስደተኞች ጉዳይ የምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት፣ የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ዋና ዲሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ፣ ኢትዮጵያ፥ ከየአቅጣጫው ስደተኞችን እየተቀበለች እንደኾነ ተናግረው፣ የርዳታ ፍላጎታቸውን ግን ማሟላት አልተቻለም፤ ይላሉ፡፡ በቅርቡ፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት(USAID) ያሳለፈው የርዳታ ማቋረጥ ውሳኔም፣ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት፣ ከላስአኖድ እና ከሱዳን የተነሡ ሁለት የተፈናቃዮች ፍልሰቶችን ማስተናገዷን የጠቀሱት ዋና ዲሬክተሩ፣ ሱዳን ትልቅ ሀገር ስለኾነች፣ ግጭቱ ከቀጠለ ብዙ ሰው ሊፈልስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አመልክተዋል፡፡ እስከ አሁንም፣ 10 ሺሕ የሚደርሱ ሱዳናውያንና በሱዳን የነበሩ ኤርትራውያን፥ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በመግባት ጥገኝነት እንደጠየቁ፣ ዋና ዲሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ የሁለቱ አካባቢዎች ፍልሰቶች፣ በበጀት ዓመቱ ያልታሰቡ በመኾናቸው፣ እነርሱን ለመርዳት፣ ተጨማሪ የርዳታ ገንዘብ ማፈላለግን የግድ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡
ኾኖም፣ ተጨማሪ ርዳታ ማግኘቱ፣ “ከባድ ኾኗል፤” ይላሉ አቶ ተስፋሁን፡፡ በዚኽ ሳቢያ፣ ለስደተኞቹ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እንደተቸገሩና በተለይም፣ ከምግብ ጋራ በተያያዘ፣ በስደተኞች ርዳታ አቅርቦት ከፍተኛ አጋዥ የነበረው ዩኤስ-ኤይድ፣ ለኢትዮጵያ ሲያቀርብ የነበረውን ድጋፍ በማቆሙ ምክንያት፣ በአሁኑ ወቅት፣ ስደተኞች ሙሉ በሙሉ ከቀለብ ውጪ እንደኾኑ አስታውቀዋል፡፡ “የላስአኖድ ስደተኞች ብቻ ሳይኾኑ፣ ሌሎቹም ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል፤” ሲሉ ዋና ዲሬክተሩ ተስፋሁን ጎበዛይ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ፣ በዋናነት፥ ከኤርትራ፣ ከሶማልያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሱዳን የመጡ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እንደምታስጠልል በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡