ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ ለረኀብ ከተጋለጡ ተፈናቃዮች ራሳቸውን ያጠፉ እንዳሉ ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

በኦሮሚያ ክልል ከምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ዞኖች አምስት ወረዳዎች ተፈናቅለው፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን “ሀሮ” በተባለ ቦታ የተሰባሰቡ ተፈናቃዮች፣ ለረኀብ መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው በነበረ ግጭት፣ ቀዬአቸውን ለቀው በምዕራብ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ልዩ ስሙ “ሀሮ” በተባለ ቦታ ላይ፣ ያለመጠለያ እንደሚገኙ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ ሰብአዊ ድጋፍ እና የሕክምና አገልግሎት፣ ከመንግሥት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በተያያዘም፣ ባለፈው ሳምንት፣ ዓለማየሁ ገብረ ሐና እና ሑሴን ፈንቴ የተባሉ ተፈናቃዮች፣ ልጆቻቸው ሲራቡ ማየት እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ራሳቸውን መርዘው እንዳጠፉ፣ ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች ተፈናቃዮች፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው ሰኔ ወር ብቻ፣ ራሳቸውን ካጠፉት ሰዎች በተጨማሪ፣ ሦስት እናቶች በወሊድ፣ ሁለት ሕፃናት ደግሞ በሕክምና ዕጦት ምክንያት እንደሞቱ፣ ተፈናቃዮቹ አስረድተዋል፡፡

በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም.፣ በአካባቢው በነበረው ግጭት ተፈናቅለው “ሀሮ” በተባለ ቦታ እንደሚገኙ የተናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ በ2014 ታኅሣሥ ወር ላይ ብቻ፣ የርዳታ እህል እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ቡሳ ጎኖፋ ወረዳ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ዳኜ ለቺሳ፣ 55 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች በወረዳው ቢኖሩም፣ በቦረና በተከሠተው ድርቅ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የርዳታ አሰጣጥ፣ ሰሞኑን ወደ ዞኑ የርዳታ እህል በመግባቱ፣ መሠራጨት እንደሚጀምር አመልክተዋል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ።