የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ቲክቶክ እንዲዘጋ የሚጠይቅ ዘመቻ ይዘዋል

Your browser doesn’t support HTML5

ቲክቶክ የተሰኘው ቁጥሩ እጅግ የበዛ ተጠቃሚ ያለውና አጭር ምስሎችን ለማጋራት የሚያስችለው የኢንተርኔት መተግበሪያ መታገድ እንደሌለበት ለማስረዳት የኩባንያው ሊቀመንበር እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሻው ዚ ቹ ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ከአባላቱ ለቀረቡላቸው ጠበቅ ያሉ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ውለዋል።

ሻው ዚ ቹ ከምክር ቤት አባላቱ ፊት በትላንትናው ዕለት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡበት ሥነ ሥርዓት የተካሔደው፥ 150 ሚሊዮን አሜሪካውያን ተጠቃሚዎች ላሉት ኩባንያቸው፣ ከፍተኛ የመረጃ እና የተጠቃሚዎች ደኅንነት አደጋ ደቅኗል፤ የሚል ሥጋት ያደረባቸው የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ግፊት እየጨመረ በመጣበት ወሳኝ ወቅት ነው።

ከወግ አጥባቂው ወገን የኾኑቱ የምክር ቤት አባላት እና አንዳንድ ተሟጋቾች፣ የምክር ቤቱ ኮሚቴ ያካሔደውን ምስክር የመስማት ሒደት ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቲክቶክ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲዘጋ ለማድረግ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።