ዳካ ውስጥ የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

Your browser doesn’t support HTML5

በባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ ውስጥ በሚገኘው ታዋቂ የገበያ ማዕከል እና የከተማዋን ጥንታዊ ሰፈሮች በጥቁር ጭስ የሸፈነውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በስፍራው ተሰማርተዋል፡፡

የእሳት አደጋው፣ እስከ አኹን በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ተረጋግጧል። “ቦንጎ ባዛር” የተባለው የገበያ ማዕከል እና በቅርብ የሚገኙ ሱቆች፣ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የሱቆቹ ባለቤቶች እና የእሳት አደጋ ሠራተኞች አረጋግጠዋል።

አደጋውን ለመቆጣጠር፣ 600 የሚደርሱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እየታገሉ መኾኑን፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ቃል አቀባይ ራኪቡል ኢስላም፣ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ ወታደራዊ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት፣ የአየር ኃይል ሄሊኮፕተሮችም እያገዙ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከአየር ላይ በተወሰደ ምስል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ኹኔታውን ሲመለከቱ ታይተዋል፡፡

የእሳት ቃጠሎ የደረሰበት የገበያ ማዕከል፣ በአገሪቱ ባሉ ፋብሪካዎች ተሠርተው ወደ አውሮፓ ገበያዎች ያልተላኩ እንደ “ቶሚፊልገር” ያሉ ታዋቂ የፋሽን ልብሶች፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጡበት ስፍራ ነው፡፡

በደረሰው አደጋ ያዘኑት የተቃጠሉት ሱቆች ባለቤቶች፣ በአገሪቱ ዐቢይ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል የኾነው “ዒድ” እየቀረበ ባለበት ወቅት፣ የእሳት ቃጠሎው በማጋጠሙ፣ ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

“1.5 ሚሊየን ታካ ወይም 14ሺሕ100 ዶላር ተበድሬ፣ ለዒድ ልብሶችን ለመሸጥ ገዝቼ ነበር፡፡ አሁን ኹሉንም አጥቻለኹ፤” ሲሉ፣ አንድ የንግድ ባለቤት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡