በአፋር ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራርን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተገደሉ

Your browser doesn’t support HTML5

በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን ሦስት የሓንሩካ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ዑመር ለማን ጨምሮ ሰባት ሰዎች፣ በታጣቂዎች ጥቃት መገደላቸው ተገለጸ። የገቢ ረሱ ዞን ሦስት የብልጽግና ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ሐሰን ዲንም፣ አቶ ዑመር ለማ እና ወንድማቸው በታጣቂዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ለዚኽ ዘገባ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ አካባቢ፣ ከትላንት በስቲያ በተሰነዘረ የታጣቂዎች ጥቃት፣ የአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን ሦስት የሓንሩካ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ አመራር አቶ ዑመር ለማን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲው በአወጣው መግለጫም፣ የታጣቂዎቹ ጥቃት የተፈጸመው፣ ከአዳማ ወደ አዋሽ በሚወስደው መንገድ ላይ እንደኾነ ጠቅሶ፣ በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል፣ የአፋር ገቢ ረሱ ዞን ሦስት የሓንሩካ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ዑመር ለማ እንደሚገኙበት አስታውቋል። ስለ ጥቃቱ ፈጻሚዎች ማንነት ግን፣ ፓርቲው በቀጥታ ያለው ነገር የለም።

የገቢ ረሱ ዞን ሦስት ብልጽግና ጽ/ቤት ሓላፊ ሐሰን ዲን ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ የ35 ዓመቱ አቶ ዑመር ለማ በታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉት፣ አባታቸውን በዐዲስ አበባ አሳክመው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ነው፡፡ በጥቃቱ የአቶ ዑመር ወንድም አብረው ሲገደሉ፣ በመኪና ውስጥ ከነበሩት አራት ሰዎች መሀከል፣ ከሕክምና በመመለስ ላይ የነበሩት የአቶ ዑመርን አባት ጨምሮ ሁለት ሰዎች መትረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ የብልጽግና ጽ/ቤት ሓላፊ አክለውም፣ የጥቃቱ አፈጻጸም፣ መንግሥት፥ ተመሳሳይ የጸጥታ ችግሮችን፣ በተቀናጀ መልኩ መከላከል እንዳለበት ያሳያል፤ ብለዋል፡፡

የሓንሩካ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ዑመር ለማ የግድያ ዜና የተሰማው፣ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ከተገደሉ ዘጠኝ ቀናት በኋላ ነው፡፡

ሟቹ አቶ ዑመር፣ ባለትዳር እና የአምስት ልጆች አባት እንደኾኑ፣ ከገቢ ረሱ ዞን ሦስት ብልጽግና ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሟቾችን ጠቅላላ ቁጥር እና ስለደረሰው ጉዳት፣ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።