የንግድ ቦታዎቻቸው የፈረሱባቸው የዐዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች “መንግሥት መፍትሔ ይስጠን” ሲሉ ጠየቁ

Your browser doesn’t support HTML5

የዐዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ በዋና መዲናዪቱ፣ የመሥሪያ ቦታቸው ለፈረሰባቸው አባላቱ፣ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው፣ ጥሪ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ገለታው ሙሉ፣ ጥያቄው፣ ለመንግሥት አካላት በየደረጃው ቀርቦ ምላሽ ስላልተሰጠው፣ በብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ ለማስተላለፍ እንደተገደዱ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በሰጠው መግለጫ፣ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች፣ የመሥሪያ ቦታዎቻቸው የፈረሱባቸው ወደ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች፣ ለከፍተኛ ችግር በመዳረጋቸውና ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጥ በመኾኑ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ሊደርስላቸው ይገባል፤ ይላል፡፡

የዐዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ የሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ፣ “የአካል ጉዳተኞቹ ጥያቄ ደርሶኛል፤ የማጣራት ሥራ አከናውናለኹ፤” ብሏል፡፡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ፣ የአካል ጉዳተኞቹን ችግር ለመፍታት ንግግር እየተደረገ እንደኾነ ገልጿል፡፡

ማኅበሩ፣ በሰሜን ሆቴል መግለጫ በሰጠበት ወቅት የተገኙት ፕሬዚዳንቱ አቶ ገለታው ሙሉ፣ በኢትዮጵያ በአኃዝ ከታወቁት አካል ጉዳተኞች፣ 98 ከመቶ ያህሉ ሥራ ዐጥ እንደኾኑና በዐዲስ አበባ የአካል ጉዳተኞችን የንግድ ቦታዎች የማፍረስ እንቅስቃሴ ችግሩን እያባባሰው እንዳለ ገልጸዋል፡፡

መግለጫውን በንባብ ያሰሙት፣ የአካል ጉዳተኞች የንግድ ማኅበራት ተወካይ አቶ ኢዮብ ደስታ፣ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች፣ የአካል ጉዳተኞቹ የመሥሪያ ቦታዎች ሲፈርሱ ቅድመ ዝግጅት እንዳልተደረገና ከፈረሱም በኋላ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዳልተሰጠ አመልክተዋል፡፡

“ዐዲስ አበባን ከሸራ ሱቆች እናጽዳ” በሚል መመሪያ፣ የመሥሪያ ቦታቸው የፈረሰባቸው ሦስት ሺሕ የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች ችግር ላይ ወድቀዋል፤ ያሉት አቶ ኢዮብ፣ መንግሥት መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዐዲስ አበባ ከተማ የሴቶች የሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከአካል ጉዳተኞቹ ጥያቄ እንደቀረበለት ገልጾ፣ “ጉዳዩን ለማየት እየሠራኹ ነው፤” ብሏል፡፡

ቀደም ሲል፣ ስለ ጉዳዩ በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት የሴቶች የሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወሮ. ዓለሚቱ ኡሞድ ደግሞ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የአካል ጉዳተኞቹን ጥያቄ መቀበሉን ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ በበኩላቸው፣ “የደረሰብን ችግር ፋታ የሚሰጥ ባለመኾኑ፣ መንግሥት ይድረስልን፤” ሲሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በቅዳሜው የመግለጫ አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት ላይ ከተሳተፉት በመቶዎች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ውስጥ የተወሰኑት፣ በዐዲስ አበባ ሰሜን ሆቴል አካባቢ መንገድ በመዝጋት፣ ጥያቄያችን ይመለስ፤ የሚል ድምፅ ማሰማታቸውን፣ የአሜሪካ ድምፅ ተመልክቷል፡፡