ዛሬ ጠዋት በአዳማ ከተማ ቀበሌ 13 አቅራቢያ በሚገኛና በተለምዶ “የጨረቃ ቤት” እየተባለ የሚጠራ መንደርን ለማፍረስ በተሰማራ ግብረ ኃይልና በነዋሪዎቹ መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ሰዎችንም በታጣቂዎች መደብደባቸውን ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገለፁ። ሟቾቹን በተመለከተ ከክልሉ መንግሥት ያገኘነው መረጃ የለም።
ዋሽንግተን ዲሲ —
ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን በአካባቢው ነበርኩ ያሉ የዐይን እማኝ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤ ዛሬ ጠዋት ፖሊስና የመዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ወደ ስፍራው ሄደው ነዋሪዎቹ እንዲወጡ ማደረጋቸውን ነው። “ነዋሪዎቹ ቤት የሚያፈርስ ግሬደር መኪና ሲመለከቱ በአንድ ጊዜ ቤት ሊፈርስባቸው እንደማይገባ ተራበሸ። ከዛ ቀስ በቀስ ተጋግሎ ወደ ተኩስ ተሸጋገረ።” ብሎናል።
ነገሩ እየተጋጋለ ሲሄድ የታጠቀ ኃይል እየተበራከተ መምጣቱን የሚናገረው ነዋሪው፤ “በረብሻው መካከል ሚሊቴሪ ኃይሎቹ ብዙ ሰዎችን ደበደቡ። በቁጥር መለየት ባልችልም ብዙ ሰው ቆስሏል። ሁለት ሰውም ተመቶ ሞቷል። አንዱ የቤት ባለቤት አንዱ ደግሞ እዛው ነዋሪ የነበረ ሰው ነው። ከዛ እዛ የነበሩ በተለይ አዛውንትና ሴቶች ሸሹ ወጣቶቹ ግን እየጮሁ ከተማውን መዞር ጀመሩ” ሲል በዛሬው ዕለት የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።
በመጨረሻ ቤቶቹ ባይፈርሱም ታጣቂዎቹ አካባቢውን በብዛት በመቆጣጠራቸው ሁኔታው መብረዱን ነዋሪው ገልፆ ቀስ እያሉ ግን እንነሱም እየተቀነሱ መሄዳቸውን ጠቁሟል። ሁኔታውን ለማጣራት የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ለማግኘት ጥረት አድርገን አልተሳካም።
በነገው ምሽት የሬዲዮ ፕሮግራማችን በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን።