በአዲስ አበባ እየተካሔደ ባለው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአንጎላውን ፕሬዝደንት ዡዋ ሎሬንሶ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸውን ተረክበዋል።
ዡዋ ሎሬንሶ ተሰናባቹን ሊቀመንበር የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ኦልድ ቼክ ጋዙዋንን ተክተዋል። ብሩንዲ፣ ጋና እና ታንዛኒያ የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር እንዲኾኑ ተመርጠዋል።
ከኅብረቱ ከታገዱት ስድስት ሀገራት በስተቀር 55ቱም የአባል ሀገራት በ38ኛው የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጭ ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት እንደተናገሩት፣ 29 ፕሬዝዳንቶች ፣ ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና አንድ ንጉስ በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል። ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት የታገዱት ስድስቱ ሀገራት ቡርኪናፋሶ፣ጋቦን፣ጊኒ፣ማሊ፣ኒጀር እና ሱዳን ናቸው።
የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ በመካሔድ ላይ የሚገኘው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት እየተባባሰ ባለበት ወቅት አማጽያን በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች እየገሰገሱ ባሉበት ወቅት ነው። የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች አስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል።
ሱዳን መሪዎቹ ሊወያዩበት ያቀዱት ሌላው የግጭቱ ዋና ማዕከል ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ሱዳን ውስጥ የሚገኙ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና የሰብአዊ ሠራተኞችን ጨምሮ ሲቪሎችን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል። ጉቴሬዥ 26 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን አስቸኳይ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች 6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቀዋል።