በጦርነት በታመሰችው ሱዳን 30 ሚሊዮን ሰዎች ርዳታ ይሻሉ

የአለም የምግብ ባንክ ከባድ መኪና እና ባልደረባ ህዳር 3/ 2017 ዓ.ም በሱዳን

ጦርነት ባደቀቃት ሱዳን አብዛኞቹ ሕፃናት የኾኑ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ርዳታ እንደሚሹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ አስታውቋል።

30.4 ሚሊዮን ከሚኾኑት ውስጥ 20.9 ለሚሆኑት 4.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ርዳታ የጠየቀው ተመድ፣ በሱዳን ያለውን ሁኔታ “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ቀውስ” ሲል ገልጾታል።

ላለፉት 20 ወራት በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ሕዝቡን ለቸነፈር አጋልጧል።

በጦርነቱ በ10ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት በሃገር ውስጥ ተፈናቅለዋል። ከጦርነቱ ቀደም ብሎም 2.7 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን፣ ይህም ሱዳንን በዓለም ትልቁ የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ያለባት ሃገር ያደርጋታል። ተጨማሪ 3.3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ሃገር ጥለው ተሰደዋል። በመሆኑም ከጦርነቱ በፊት ይገመት ከነበረው 50 ሚሊዮን የሱዳን ሕዝብ ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆነው ተፈናቅሏል።

በአምስት አካባቢዎች ረሃብ የታወጀ ሲሆን፣ እስከ መጪው ግንቦት ድረስ ተጨማሪ አምስት አካባቢዎች ለረሃብ እንደሚጋለጡ ይገመታል። 8.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቅርቡ ረሃብ ሊገጥማቸው እንደሚችል ተነግሯል።

በሱዳን ሠራዊት የሚደገፈው መንግሥት ረሃብ መግባቱን ሲያስተባብል፣ ረድኤት ድርጅቶች ደግሞ የቢሮክራሲ ማነቆ እና ሁከት ለተጎጂዎች እንዳይደርሱ ማድረጉን ይናገራሉ።

የሱዳን ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኅይሉ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም ክስ ይቀርብባቸዋል።

በሱዳን የሚካሂደው ጦርነት ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም፤ በመካከለኛው ምሥራቅና በዩክሬን በሚካሄዱት ጦርነቶች ምክንያት “የተረሳ ጦርነት” እንደሆነ ይነገራል።