የአልቤኒያ መንግሥት ቲክ ቶክን ለአንድ ዓመት እንደሚዘጋው አስታወቀ

ፎቶ ፋይል - የቲክ ቶክ አርማ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በኮምፒዩተር ስክሪን ፊት ለፊት የቲክ ቶክ መነሻ ገጽ። በቦስተን፣ ማሳቹሴትስ ውስጥ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር መጋቢት 18/2023 ዓ.ም.

የአልቤኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች አንዱ የኾነው ቲክቶክ፣ ግጭት ቀስቃሽ እና በተለይ ሕፃናትን የሚያሸማቅቁ ቪዲዮች የሚሰራጭበት በመኾኑ መንግሥታቸው ለአንድ ዓመት እንደሚዘጋው ትላንት ቅዳሜ ታኅሣሥ፣ 12 ቀን 2017 ዓ.ም አስታወቁ።

በቲክቶክ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ አንድ አዳጊ፣ በሌላ አዳጊ በስለት መገደሉን ተከትሎ የአልቤኒያ ባለሥልጣናት ከ1 ሺሕ 300 መምሕራንና ወላጆች ጋራ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተናገሩት የአልቤኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ፣ ቲክቶክ በአልቤኒያ ሪፐብሊክ ውስጥ እንደማይኖርና ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጋ ተናግረዋል። የመዝጋቱ ሂደትም በመጪው ዓመት እንደሚጀምር አስታውቀዋል። ቲክቶክ አልባኒያ ውስጥ ወኪል እንዳለው አልታወቀም።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት የተጠየቀው ቲክቶክ ቅዳሜ ዕለት በሰጠው የኢሜል ምላሽ፣ በስለት ተወግቶ ስለተገደለው አዳጊ የአልቤኒያ መንግሥት በአስቸኳይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል። ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለውም ኾነ፣ ድርጊቱ የተፈጸመበት ተጎጂ አዳጊ የቲክቶክ ገጽ እንደነበራቸው የሚያሳይ አንድም መረጃ እንደሌለ በኢሜል ያስታወቀ ድርጅቱ ፣ "እንደውም ብዙ ሪፖርቶች እንዳረጋገጡት ወደ አደጋው እንዲያመራ ምክኒያት የኾነው ቪዲዮ የተሰራጨው በሌላ የትስስር ገጽ ላይ እንጂ በቲክቶክ አይደለም" ብሏል።

አልቤኒያ ውስጥ ከቲክቶክ ተጠቃሚዎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሕፃናት መኾናቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ልጆች ቲክቶክ ላይ በሚያዩዋቸው ግጭት ቀስቃሽ ቪዲዮዎችና የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ትምሕርት ቤት በሚሄዱበት ጊዜ እንደ ቢለዋ ያሉ ስለት ነገሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየያዙ መሄድ በመጀመራቸው ወላጆችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

ቲክቶክ በተመሰረተበት ቻይና "በተሻለ ሁኔታ እንዴት ማጥናት እንደሚቻል፣ ተፈጥሮን እንዴት መንከባከብ እንደሚቻል እና የመሳሰሉትን በጎና የተለዩ መልዕክቶች ናቸው የሚተላለፉት" ሲሉ የአልቤኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራማ ተናግረዋል። ራማ ቲክቶክ እንዲዘጋ ያሳለፉትን ውሳኔ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አልተቀበሉትም።