በሱዳን ምዕራብ አል- ፋሽር ከተማ በሚገኘው ዋና ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት፣ ታካሚዎችና አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች መቁሰላቸውን የዓለም የጤና ድርጅት /WHO/ አስታወቀ።
የድርጅቱ ዲሬክተር ዶ.ር. ቴድሮስ አድኻኖም፣ በሱዳን በጤና ተቋማት ላይ የቀጠለው ጥቃት አስከፊ መኾኑን በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ በማጋራት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ለሁሉም ታካሚዎች እና የጤና ባለሞያዎችም ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በጤና ተቋማት እና በአካባቢው የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙም በጽሑፋቸው አሳስበዋል።
በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሃን መካከል ፣ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተጀመረው ጦርነት ሱዳን እየወደመች ነው።
ጦርነቱ በአስር ሺሕዎች ሚቆጠሩ ሲቪሎችን ህይወት ቀጥፏል፣ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል። በተጨማሪም ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ ዳርጓታል።
ሰሜናዊ ዳርፉር ዋና ከተማ አል- ፋሽርን ከግንቦት ጀምሮ በፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ ከተከበበች በኋላ ቦታው ለንግድና ለርዳታ አቅርቦት ዝግ ኾኗል።