ሀሙስ ዕለት የዩክሬይን ከተማ ዲኒፕሮ የመታው የሩስያ ሚሳይል “ለ15 ደቂቃ የተምዘገዘገ ሲሆን እኤአ ባለፈው መጋቢት 11 ከተተኮሰው የሚፈጥን ነው” ሲል የኪየቭ ከፍተኛ የስለላ ድርጅት ዓርብ ዕለት ተናግሯል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀሙስ ዕለት እንደተናገሩት ሞስኮ “ኦሬሽኒክ” ተብሎ በሚጠራውና ከድምጽ በአምስት እጥፍ ይፈጥናል በተባለው አዲስ የ“ሃይፐርሶኒክ መካከለኛ ርቀት ተጓዥ ባለስቲክ ሚሳይል የዩክሬንን ወታደራዊ ተቋም አጥቅቷል ብለዋል፡፡
"ይህ የሩስያ ሚሳይል ወደ አስትራካን ክልል ከተተኮሰበት ጊዜ አንስቶ በዲኒፕሮ ከተማ ላይ ጉዳት እስካሳደረበት ጊዜ ድረስ የፈጀው የበረራ ጊዜ 15 ደቂቃ ነበር" ሲል የዩክሬን ዋና የመረጃ ዳይሬክቶሬት ባወጣው መግለጫው ተናግሯል።
ሚሳይሉ እያንዳንዳቸው ስድስት ፈንጂዎችን የሚተፉ ስድስት ወንጫፊዎች የታጠቀ ሲሆን በመጨረሻው የመወንጨፊያ ሰዓትም ያሳየው ፍጥነት ከድምጽ በ11 እጥፍ የፈጠነ ነበር “ብሏል፡፡
የደህንነት ማዕከሉ አክሎም መሣሪያው “‹ከድር› ሚሳይል ተብለው ከሚጠሩ አዳዲሶቹ የሩሲያ ሀገር አቋራጭ ሚሳይሎች መካከል ሳይሆን አይቀርም” ብሏል።
ኪቭ መጀመሪያ ላይ “ሩሲያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ተኩሳለች” ብትልም የአሜሪካ ባለስልጣናት እና ኔቶ ግን፣ ፑቲን መሣሪያውን እንደ መካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳይል አድርገው የገለጹበትን መንገድ ተጠቅመዋል፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለጥቃቱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ትላንት ሃሙስ አሳስቧል።
ኔቶ በሞስኮ ጥቃት ላይ ለመምከር በብራሰልስ በሚገኘው የሕብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ የኔቶ ምንጭ ዛሬ አስታውቋል፡፡