የትግራይ ክልል አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፕሪቶሪያ በተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የሰፈሩ ቁልፍ ጉዳዮች በመንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ተፈጻሚ አልሆኑም አሉ።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ስምምነቱን ተፈጻሚ አለማድረግ በኢትዮጵያ ብሎም በቀጠናው “ሊንሰራፋ የሚችል” ያሉትን አሉታዊ ውጤት እንደሚያስከትል ተናግረዋል። “ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጣቸውን የትግራይግዛቶች ወደ ነበሩበት መመለስ ላይ እብዛም ለውጥ አልታየም። መላው ምዕራብ ትግራይ አሁንም በአማራ ኃይሎችቁጥጥር ስር ሲሆን በአንጻሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ” በማለት በኤክስ ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ትላንት ቅዳሜ አስፍረዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ አክለውም “የኤርትራ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ እና በምሥራቅ ትግራይ የያዟቸውን አንዳንድ ቦታዎች እንደያዙ ቀጥለዋል። በእነዚህ አካባቢዎችም በሰዎች ላይ ግፍ መፈጸሙ የተለመደ ነው። በዚህ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በማይታሰብ አስከፊ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ መጠለያ ካምፖች ውስጥ እየማቀቁ ይገኛሉ” ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የአማራ ክልል ቃል አቀባይ አቶ መንገሻ ፈንታውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የኢትዮጵያ መንግስት ለአቶ ጌታቸው ረዳ አስተያየት በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም። ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያው የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ መንግስት ‘አወዛጋቢ አካባቢዎች’ ብሎ በሚጠራቸው ምዕራባዊ ትግራይ ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት የአካባቢው ተወላጆች የራሳቸውን እድል በራሳቸውን እንዲወስኑ መሻቱን አስታውቋል።
በሌላ በኩል ኤርትራ ሰራዊቶቿ በትግራይ ክልል ውስጥ እንደማይገኙ አስታውቃለች። “ለእነዚህ የውሸት እና አሳሳችውንጀላዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ምላሽ ሰጥተናል” በማለት የኤርትራው የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ዛሬ እሁድ ተናግረዋል።
“ሰሜናዊ እና ምሥራቃዊ ትግራይ ተብለው እየተጠቀሱ ያሉት ባድሜና ሌሎች የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛቶች ሲሆኑ፤ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን በኩል የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት ተብለው የተካተቱ፤ አለም አቀፍ ህግን በመጣስ ለሃያዓመታት ያህል በወረራ ተይዘው የቆዩ ስፍራዎች ናቸው” በማለት ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሪቶሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት በትግራይ ክልል ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰላምን በማምጣት ውጤታማ ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት የባንክ፣ የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የምድር እና የአየር መጓጓዣ አገልግሎቶችን በመመለሱ ረገድ እርምጃዎች መውሰዱን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መንግስት በተሳለጠ መልኩ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የትግራይ ክልል ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቃለች። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የፕሪቶሪያውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ “መንግስት በትግራይ ክልል ከሀገሪቱ ሰራዊት ውጭ ያሉ ኃይሎችን በሙሉ እንዲያሰወጣ” አሳስቧል።
በጎርጎርሳዊያኑ ህዳር ሁለት 2022 በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በፕሪቶሪያ የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት “በዋናነት በትግራይ ክልል የመሳሪያ ድምጾች ጸጥ ብለዋል፣ የቆሙ አገልግሎቶች በድጋሚ ተጀምረዋል፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም ተመልሰዋል” በማለት ዩናይትድ ስቴትስ ሂደቱን በመልካም ተቀብላዋለች ሲል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው አስታውቋል፡
በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እንዲፈቱ ጥሪ አድርጋለች።