ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ግንኙነቷን በማጥበቅ ላይ ትገኛለች

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባድር አብዲላቲ

ዛሬ እሁድ በጅቡቲ እየተካሄደ ባለው የቱርክ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እና ፍልስጤማዊያንን በዲፕሎማሲ ለመደገፍ ጥሪ አድርጋለች።

ሀገሪቱ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ በአፍሪካ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች ሲሆን፤ የቱርኩ መሪ ረጂብ ጣይብ ኤርዶዋንም ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው አስርት ዓመታት ፤ በ31 የአፍሪካ ሀገራት 50 የሚደርሱ ጉብኝቶችን አድርገዋል።

በአሁን ሰዓት በጂቡቲ እየተካሄደ በሚገኘው የቱርክ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ አንጎላ፣ ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ኮንጎ ሪፐሊክ፣ ግብጽ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋና፣ ሞሪታኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌን ጨምሮ 14 የአፍርካ ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባድር አብዲላቲ ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ ባለፈው የጎርጎርሳዊያኑ ዓመት 35 ቢሊየን ዶላር እንደነበረ ገልጸው፤ ሀገራቸው በአፍሪካ ላይ በቀጥታ የምታፈሰው መዋዕለ ንዋይም ሰባት ቢልየን ዶላር ደርሷል በማለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቱርክ በሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሀገራት የታጠቁ ሃይሎችን በማሰልጠን እና መሳሪያ በማስታጠቅ በአህጉሪቱ አራተኛዋ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ሆናለች። ባለፉት ቅርብ ወራትም በኢትዮጵያን እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስታረቅ እንዲሁም በኒጀር የመዓድን ስምምነት ውሎችን እንዲካሄዱ ማገዟ ይታወሳል።

ቀጣዩ የቱርክ አፍሪካ ጉባኤ በጎሮጎሮሳዊያኑ 2026 እንደሚደረግ ተገልጿል።