የቡድን ሰባት መከላከያ ሚንስትሮች ጉባኤ ተጀመረ

የጣሊያኑ መከላከያ ሚኒስትር እና የካናዳው መከላከያ ሚኒስትር (ከግራ ወደ ቀኝ ) ጥቅምት 09/2017

በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት እየተባባሰ እና የዩክሬን ጦርነት ሦስተኛ ክረምቱን እየያዘ ባለበት በዚህ የውጥረት ወቅት የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መከላከያ ሚንስትሮች ጉባኤ በጣሊያን ተጀምሯል።

የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ወቅታዊ ፕሬዝዳንትነቱን የያዘችው ጣሊያን የሰሜን አትላንቲክ የቃልኪዳን ጦር ኔቶ መቀመጫ በሆነችው ኔፕልስ ጉባኤውን እያስተናገደች ነው።

ለኔቶ ሀላፊ ማርክ ሩቴ እና ለአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ለሆኑት ጆሴፍ ቦሬል እንዲሁም ለጉባኤው ታዳሚዎች አቀባበል ያደርጉት የጣሊያኑ የመከላከያ ሚንስትር ጉዓዶ ክሮሴቶ “ዛሬ እዚህ መሰባሰባችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ለመገደብ ለሚጥሩ ሁሉ ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል።

ጉባኤው በዋናነት የዩክሬን ጦርነት ላይ ትኩረቱን ቢያደርግም በአፍሪካ እና በፓስፊክ እስያ የጸጥታ ጉዳዮችም ላይ የሚወያይ ይሆናል።