በዶናልድ ትረምፕ ላይ ሁለተኛ የግድያ ሙከራ ተደረገ፣ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታወቀ

የግድያ ሙከራውን ተከተሎ የ ኤፍ ቢ አይ እና ሌሎች የፀጥታ ዓባላት በምዕራብ ፓልም ቢች፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው የትረምፕ ዓለም አቀፍ የጎልፍ ክለብ በሥራ ላይ (ፎቶ ኤ ኤፍ ፒ መስከረም 16፣ 2024)

በዶናልድ ትረምፕ ላይ ሁለተኛ የግድያ ሙከራ ተደረገ

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታወቀ

በሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንታዊ እጩና እና በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ የግድያ ሙከራ በመፈጸም የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል።

ዶናልድ ትረምፕ በባለቤትነት በያዙት በፍሎሪዳ በሚገኝ የጎልፍ ክለብ በመጫወት ላይ ሳሉ ነበር የተኩስ ድምጽ የተሰማው። ግለሰቡ ራያን ወስሊ ራውት መሆኑንና በሙከራው ወቅት ቢርቅ ከትረምፕ 457 ሜትር ላይ ይገኝ እንደነበርም ታውቋል።

የሕግ አስከባሪዎችና የፕሬዝደንቱ ልዩ የጥበቃ ቡድን (ሲክረት ሰርቪስ) ኤ ኬ 47 የታጠቀ ግለሰብ በአቅራቢያው አነጣጥሮ ሲመለከቱ ወደ ግለሰቡ እንደተኮሱ የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ማስታወቃቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

ግለሰቡ መሣሪያውን እና ሻንጣውን ጥሎ በኒሳን መኪና ሲያመልጥ አንድ የዓይን ምስክር ፎቶ ግራፍ በማንሳቱና መረጃው በአካባቢው ለሚገኙ ሕግ አስከባሪዎች በመሰራጨቱ የፀጥታ ኃይሎች ተከታትለው ይዘውታል።

ዶናልድ ትረምፕ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ሲያስታውቁ፣ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም የዲሞክራቲክ ፓርቲው ፕሬዝደንታዊ እጩ የሆኑት ካመላ ሄሪስ፣ ዶናልድ ትረሞ ላይ ጉዳት ባለመድረሱ እፎይታ እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።

“ሁከት በአሜሪካ ቦታ የለውም” ብለዋል ካመላ ሄሪስ በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት።

በዶናልድ ትረምፕ ላይ ባለፈው ሐምሌ በፔንሲልቪኒያ በተፈጸመው የግድያ ሙከራ ጥይቱ ጆሯቸውን ጨርፎት እንደነበር ይታወሳል።