ቦሌን በአራት እጥፍ ይልቃል የተባለ የአየር ማረፊያ ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

Your browser doesn’t support HTML5

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአፍሪካ ግዙፍ ያለውን የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለማስጀመር፣ ዛሬ ዐርብ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ዳር ከተባለ ኩባንያ ጋራ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ከዐዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የሚገነባው ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ በአምስት ዓመት የሚጠናቀቅ ሲኾን፣ ግንባታው በሁለት ምዕራፎች እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡

ከዳር ኩባንያ ጋራ ስምምነት የተፈረመው፣ አጠቃላይ የዲዛይንና የቁጥጥር ሥራዎችን እንዲያከናውን መኾኑን የተናገሩት አቶ መስፍን ጣሰው፣ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ የማማከር ሥራም ያከናውናል፤ ብለዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው፣ በብድር በተገኘ ገንዘብ እንደሚገነባና ከዐዲስ አበባ ጋራ በፈጣን የባቡር መንገድ እንደሚተሳሰርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል፡፡

የኩባንያው ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች፣ ዐዲሱ ኤርፖርት የሚገነባበትን ስፍራ ትላንት ኀሙስ መጎብኘታቸውም ተገልጿል፡፡

ኤርፖርቱ ከሚገነባበት ስፍራ ለሚነሡ 2ሺሕ500 የሚደርሱ አርሶ አደር አባወራዎች የሚሰፍሩበትን ተለዋጭ ቦታ፣ አየር መንገዱ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር መረከቡን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ለተነሺዎች የመኖሪያ ቤት ከመገንባት ጀምሮ ለመተዳደሪያቸው የሚኾኑ ልዩ ልዩ ተግባራት በአየር መንገዱ እንደሚከናወኑ የጠቀሱት አቶ መስፍን ጣሰው፣ ለዚኽም በጀት ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡