የህወሓት አመራሮች ጉዳይ

Your browser doesn’t support HTML5

በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) የፖለቲካ አመራር መካከል ያለው አለመግባባት ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መፈረም ከቆመ በኋላ እየሰፋ መምጣቱን፣ አመራሮቹ የሚሰጧቸው የተናጠል መግለጫዎች ያመለክታሉ፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ባለፈው ሰኞ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ለድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በፓርቲው ውስጥ ልዩነቶች እየሰፉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይኸው ልዩነት፣ በህወሓት የፖለቲካ አመራሮች እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል፣ አንድነት እና መግባባት እንዳይኖር ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡

በመዋቅሩ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በርከት ያሉ የህወሓት አባላትን ያካተተው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን፣ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ዕንቅፋት እንደኾነበት፣ አቶ ጌታቸው በሰኞው ቃለ መጠይቃቸው ተናግረዋል፡፡ ፖለቲካዊ መጠላለፉ፣ እርሳቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩን መሪነት እንደተረከቡ ወዲያውኑ መጀመሩን አውስተው፣ የህወሓት ጽሕፈት ቤት፣ የተደራጀ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደከፈተባቸውም ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው፣ ለድምፀ ወያነ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በህወሓት አመራሮች መካከል፣ ልዩነቶች እና ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች እየበረቱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ እነዚኽ ችግሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩን በአግባቡ እንዳይሠራ አድርገውታል፤ ብለዋል፡፡

ህወሓትም፣ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ፣ በፓርቲው ውስጥ ችግር ማጋጠሙንና በአመራሩም ዘንድ መከፋፈል እንዳለ አስታውቋል፡፡ ፓርቲው ያካሔደውን የከፍተኛ አመራር ስብሰባ መጠናቀቅ በማስመልከት፣ ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በንባብ ያሰማውና በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ያሰፈረው መግለጫ፣ አሁን የተጋረጠበት አደጋ በ50 ዓመት ታሪኩ ውስጥ አይቶት የማያወቅ እንደኾነ አመልክቷል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሞያ አቶ ተኽሊት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፣ ፓርቲው፥ “የህወሓት ጽሕፈት ቤት” እና “የጊዜያዊ አስተዳደር” በሚሉ ሁለት ቡድኖች መከፈሉን አንሥተው፣ “አለመግባባቱ በጊዜ ካልተፈታ የከፋ መዘዝ ያስከትላል፤” ብለዋል፡፡