በኢትዮጵያ አዲስ በተከሰተ የመሬት ናዳ 11 ሰዎች ሞቱ

በካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ የደረሰው የመሬት መናድ (ፎቶ: የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ 08/05/2024)

በወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ ዛሬ ሰኞ በደረሰ የመሬት ናዳ 11 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልታናት እንዳስታወቁ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

አደጋው የደረሰው ከሳምንት በፊት ተመሳሳይ አደጋ ደርሶ ከ250 ሰዎች በላይ ሕይወታቸውን ካጡበት ከንቾ ሻቻ ጎዝዲ በቅርብ ርቀት ላይ መሆኑም ታውቋል።

እስከ አሁን የ 11 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንና የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የካዎ ኮይሻ ወረዳ አስተዳደር መግለፁን የወረዳው መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ማስታወቁን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

በአካባቢው በሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ተደጋጋሚ የመሬት ናዳ እየተከሰተ ይገኛል።

በሲዳማ ክልልም በተመሳሳይ በቅርቡ በደረሰ አደጋ 11 ሠዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የጎርፍ እና የመሬት ናዳ አደጋ ስጋት በመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአካባቢው ባለሥልጣናት አሳስበዋል።