ወታደራዊ ግዳጅ ያበረታቸው የፈረንሳይ ወታደሮች  የፓሪስ ኦሊምፒክ ጥበቃውን ተያይዘውታል

  • ቪኦኤ ዜና

የፈረንሳይ ወታደሮች በጥበቃ ላይ

የፓሪስ ኢሊምፒክ የተጀመረው ከጥቂት ቀናት በፊት ነው፡፡ ፈረንሳይ ከወዲሁ በባቡር መሥመሮቿ እና በኢንተርኔት አገልግሎቷ ላይ ጥቃት አስተናግዳለች፡፡ ቢሆንም በብዙ አስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች እና የጦር ሠራዊት ወታደሮች ጸጥታ እንዲያስከብሩ አሰማርታለች፡፡

በሰሜን ምስራቃዊው የፓሪስ አካባቢ ለመዲናዋ የጸጥታ ጥበቃ የተመደቡት ፖሊሶች እና ወታደሮች በጠዋቱ እየተዘዋወሩ ጥበቃውን ተያይዘውታል፡፡ አብዛኛው የፓሪስ ነዋሪ ለበጋ የዕረፍት ጊዜው ሊዝናና ወደተለያየ ቦታ ሄዷል፡፡ የወትሮ ጎብኚዎችም የሉም፡፡ ቢሆንም ወታደሮች ከተማዋን በንቃት እየጠበቁ ናቸው፡፡ሳጂን ያን የአንዱ የጥበቃ ቡድን አለቃ ሲሆን ለማንኛውም ለሚከሰት ነገር ዝግጁ ሆነን በንቃት እንጠብቃለን፡፡ አንዳች የሚያሰጋ ነገር ቢከሰት አለን፡፡ ነዋሪዎች ችግር አጋጥሟቸው ከፈለጉንም እንገኛለን” ብሏል፡፡

ወታደሮቹ በፓሪስ ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፍረዋል፡፡ እነዚህ የአየር ወለድ ወታደሮች ከኢራቅ ወይም ከሳህል አካባቢ ሀገሮች ግዳጃቸው ላይ ተጠርተው የመጡ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ግዳጃቸው ያጠናቀቁም አሉባቸው፡፡ ዋና ሳጂን ቻርሊ ጋቦን፡ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፡ አይቮሪኮስት እና ማሊ አገልግሏል፡፡ የማሊ ቆታው አስቸጋሪ እንደነበረ ይናገራል፡፡ሦስት ወር ሙሉ ያለማቋረጥ በጸረ ሽብርተኛ ተልዕኮ ማሊን ኒዠርን እና ቡርኪና ፋሶን በሚያዋስነው በረሃማ የድንበር አካባቢ አሳልፏል፡፡

ወታደሮቹ ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት የጀመሩ እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጥበቃ ላይ ናቸው፡፡ “ “ብዙ ሕዝብ ስላለ መጠበቅ አለብን፡፡ የባቡር ጣቢያው ፡ ሴን ወንዝ፡ የኦሊምፒክ ታዳሚዎች ያሉበት ቦታ ሁሉም መጠበቅ አለበት”ብሏል ዋና ሳጂን ቻርሊ፡፡

ሻምበል ኮሬንቲን “ ኦሊምፒክስ ጥበቃ ላይ በበመደቤ በጣም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ፓሪስ ኦሊምፒክ ካስተናገደች ወደ 100 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስለዚህ በሕይወት አንድ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር ነው” ብሏል፡፡