አዲስ የ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ከስምምነት ላይ መደረሱን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤም ኤፍ ትላንት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ‘የድርጅቱን ድጋፍ ለማግኝት እና ለረጅም ጊዜ ሳይከፈል የቆየ የዕዳ መክፈያ መዋቅሩን ለማሻሻል የታለመ ነው’ በተባለ ርምጃ የአገሪቱ የብር ምንዛሪ ግብይት አሠራር በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል በሚደረግ የምንዛሪ ልውውጥ የሚወሰንበትን የገበያ ሥርዓት የሚከተል መሆኑን በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በዓለም የገንዘብ ድርጅት የተደገፈው እና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2019 ዓ.ም. ተደርሶ የነበረው የመጨረሻው የብድር መርሃ ግብር በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ከተተወ በኋላ የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ ካለፈው ዓመት አንስቶ በሁለቱ ወገኖች መካከል አዲስ የብድር መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ንግግር ሲደረግ መቆየቱም የሚታወቅ ነው።
አዲሱም ስምምነት ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወዲያውኑ መላክ የሚያስችል መሆኑን አይኤምኤፍ ይፋ አድርጓል።
እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እና ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የምጣኔ ሃብት ይዞታዋን ክፉኛ የደቀባት ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ካሁን ቀደም የውጭ ብድር እዳቸውን መክፈል ተስኗቸው የቆዩ የአፍሪቃ ሃገሮችን በመቀላቀል ሦስተኛዋ አገር መሆኗ ይታወሳል።
በአፍሪካ በሕዝቧ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በድርጅቱ አሠራር መሰረት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የዕዳ ማሻሻያ ጥያቄ ብታቀርብም፣ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ተጓቶ መቆየቱ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተንታኞች ከአይኤምኤፍ ጋራ ከያዘው ድርድር ጋራ የተያያዘ ነው ያሉትን በወለድ የተመን ሥርአት ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲውን ጨምሮ አንዳንድ የምጣኔ ማሻሻያዎችን ማድረጉን በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ማመላከቱም ተዘግቧል።