በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው፣ ጃዳል ሻምስ በተባለ ቦታ ትላንት ለደረሰውና 12 ሕጻናት እና አዳጊዎች ለተገደሉበት ጥቃት ሂዝቦላን ተጠያቂ ያደረገችው እስራኤል፣ የበቀል ርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
በሌላ በኩል በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች የቀብር ሥነ ስርዓት፣ ዛሬ በሺዎች የተቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ተከናውኗል።
ሂዝቦላ በሲቪሎች ጥቃት ላይ እንዳልተሳተፈ በመግለጽ አስተባብሏል። መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የእስራኤል ሃማስ ጦርነት በጋዛ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ፣ጦርነቱ ወደ ብዙ የተለያያዩ ግንባሮች የተስፋፋ ሲኾን፣ የትላንቱ ጥቃት በእስራኤል እና ሂዝቦላ መካከል እየጨመረ ያለውን ውጥረት እንደሚያሰፋው ተሰግቷል።
እስራኤል የበቀል ርምጃ እንደምትወስድ ካስጠነቀቀች በኋላ፣ ለሊት ላይ ጄቶቿ ደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢን ደብድበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታንያሁ የዩናይትድ ስቴትስ ጉብኝታቸውን አቋርጠው መመለሳቸውን ተከትሎ፣ ከጸጥታው ምክር ቤት ካቢኔዎቻቸው ጋራ የሚያደርጉትን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ ጠበቅ ያለ ርምጃ ሊኖር ይችላል በሚል ተሰግቷል።
ሂዝቦላ መጀመሪያ ላይ በጎላን ተራራ አካባቢ በሚገኙ የእስራኤል ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ሮኬቶች መተኮሱን አስታውቆ የነበረ ቢኾንም፣ ማጅዳል ሻምስ ውስጥ 12 ሕጻናት እና አዳጊዎች ከተገደሉበት ጥቃት ጋራ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጓል።
ይሁን እንጂ የሮኬቱ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከደቡብ ሊባኖስ ቼባ መንደር ከተሰኘ አካባቢ መኾኑን የገለጸችው እስራኤል፣ "ጥቃቱ በኢራን በሚደገፈው የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድን መፈጸሙ የተረጋገጠ እና የማያሻማ ነው" ብላለች።