የደመቀው የፓሪስ ኦሊምፒክስ መክፈቻ ሥነ ስርዓት

አርብ ሐምሌ 19 ቀን 2024 ዓ.ም. ፓሪስ ውስጥ የተካሄደው የኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነ ስርዓት

ፓሪስ አርብ ሐምሌ 19 ቀን 2024 ዓ.ም. የሴይን’ን ወንዝ ተከትሎ ባለው ሥፍራ እጅግ ባማረ እና በከዋክብት በደመቀ እና ታሪካዊ የውበት እና የለውጥ መፍለቂያ ስሟን ያንጸባረቀ ልዩ ዝግጅት በመቶ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያዋ በሆነው የበጋ ኦሎምፒክ መክፈቻ አድምቃ አምሽታለች።

ቆም መለስ በሚለው ዝናም እና በፈጣን የመመላለሻ ባቡሮች የሀዲድ መስመሮች ላይ የደረሰው የተቀናጀ የእሳት ቃጠሎ በመጓጓዣዎች ላይ መጠነ ሰፊ መስተጓጎል ቢያስከትልም፤ ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ የሴይን ወንዝን ዳርቻ ተከትሎ ባለው ሥፍራ፤ በሰው ብዛት በተጨናነቁ ድልድዮች እና በሕንጻዎች ሰገነት ላይ ሆኖ የኦሎምፒክ ቡድኖች በጀልባዎች ተሳፍረው ያሳዩትን ትርኢት ተከታትሏል።

"ዝናቡ ሊያስቆመን አይችልም" ያለው የዩናይትድ ስቴትሱ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ተጫዋች ሌብሮን ጀምስ የሃገሩን ባንዲራ አንግቦ ካጀበው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ኮኮ ጋውፍ ጋራ በመኾን የትርኢቱ ተካፋይ ሆኗል።

የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደንን ጨምሮ የበርካታ ሐገሮች መሪዎች እና የመንግሥት ተወካዮች በሥፍራው ተገኝተዋል። አሜሪካዊቱ ሌዲ ጋጋ በፈረንሣይኛ ስትዘፍን፣ ሴሊን ዲዮን’ም የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን ካደመቁ ድምጻዊያን አንዷ ሆናለች።

በዓለም ዙሪያ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሚጫወቱ ድምጻውያን ከፍተኛ ተደማጭነት ያላት ማሊያዊ-ፈረንሳይቱ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ አቀንቃኝ አያ ናካሙራ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሳ፣ በዳንሰኞቿ እና እንዲሁም በፈረንሳይ ብሄራዊ የክብር ዘብ ባንድ ታጅቦ ተወዳጁን "ጃጃ" የተሰኘ ሙዚቃዋን ተጫውታለች።

የመክፈቻ ሥነ ሥርአቱ መታየት ከጀመረ ከሦስት ሰአት በኋላም የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ውድድሩ በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል። የፓሪስ ኦሊምፒክ እኩል ቁጥር ያላቸው ወንድ እና ሴት አትሌቶች በውድድሩ ሲሳተፉ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።