ሩሲያ የዩክሬን ደቡባዊ ኬርዞን አካባቢ ደበደበች

  • ቪኦኤ ዜና

ሩሲያ የዩክሬን ደቡብ አካባቢ በሚገኘ ኬርዞን ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ የታየው ፍንዳታ።

የሩሲያ ኃይሎች በደቡባዊው የዩክሬን ኬርዞን ክፍለ ግዛት ያሉ በርካታ መጠለያዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ማድረሷን የዩክይን ባለሥልጣናት ገለጹ። ሩሲያ በሰው አልባ አውሮፕላን ባደረሰችው ጥቃት አንድ አምቡላንስ መትታ አሽከርካሪውን ማቁሰሏን አመልክተዋል።

የሩሲያ ኃይሎች በተጨማሪም በመላዋ ዩክሬን በሚገኙ አራት ክፍለ ግዛቶች ቢያንስ በሚሳይል እና በአስራ አንድ ድሮኖች ጥቃት መሰንዘራቸውን ያመለከተችው ዩክሬን አየር ኃይሏ፣ ሁሉንም መተው እንዳከሸፉት አስታውቃለች።

በሌላ በኩል ዛሬ ቀደም ብሎ ዩክሬን በሩሲያ የድንበር አካባቢዎች ላይ ያነጣጠሩ 20 የድሮን ጥቃቶች እንደሰነዘረች የተናገሩት የሩስያ ባለሥልጣናት ቢያንስ አስራ አራቱን መተናቸዋል ብለዋል።

በሩሲያ ኩርስክ አካባቢ የዩክሬን ድሮን በጣለው ፈንጂ ቢያንስ 2 ሰዎች ማቁሰሉን የሩሲያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች በአየር ኃይሎቻቸው እና በሰው አልባ በራሪዎች ጥቃቶቻቸውን የቀጠሉት ዩክሬን ከሩስያ ጋራ በሚያዋስናት የ1 ሺሕ 100 ኪሎ ሜትር ድንበር እየገፋ ያለውን የሩሲያ ጥቃት ለመመከት እየተቸገረች ባለችበት በዚህ ወቅት መሆኑ ነው።