"የሀገራችንን አንድነት ለመጠበቅ የተሻለው መንገድ ችቦውን ለዐዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ ነው" ፕሬዝደንት ባይደን

  • ቪኦኤ ዜና

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን በተመለከተና “ወደፊት ስለሚሆነው” እንዲሁም “ለአሜሪካ ሕዝብ በመከወን ላይ ያሉትን ሥራ እንዴት እንደሚያጠናቅቁ” እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለአሜሪካ ሕዝብ ንግግር አድርገዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከፕሬዝደንታዊ ምርጫው ፍክክር በድንገት ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማብራሪያ የሰጡበትን ንግግር ዛሬ ምሽት አድርገዋል።

በአሜሪካ ፖለቲካ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ፕሬዝደንቱ ከኋይት ሐውስ "ኦቫል ኦፊስ" ጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ንግግር "ይህንን ጽሕፈት ቤት እጅግ በጣም አከብረዋለሁ፣ ነገር ግን ሀገራችንን ከእርሱ በላይ እወዳታለሁ" ብለዋል።

"የሀገራችንን አንድነት ለመጠበቅ የተሻለው መንገድ ችቦውን ለዐዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ ነው" ሲሉ በንግግራቸው መልዕክት ያስተላለፉት ጆ ባይደን፣ ለዐዲስ ትውልድ ቦታውን መልቀቅ የተሻለ ነው ብለው መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የ81 ዓመቱ ባይደን ከሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ተፎካካሪው ከቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ጋራ ካደረጉት ያልተዋጣ ክርክር በኋላ፣ በቀጠሉት ሳምንታት ዲሞክራቶች ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ቢወተውቷቸውም አሻፈረን ብለው የከረሙ ሲኾን በአንድ ወቅት "እሱን የማደርገው እግዚአብሔር አድርግ ካለኝ ብቻ ነው" ማለታቸው ተጠቅሷል።

ባይደን በፕሬዝደንትነት በድጋሚ ለመመረጥ ከሚያደርጉት የምርጫ ፉክክር በድንገት ራሳቸውን ካገለሉ እና ቦታውን እንዲወዳደሩበት ምክትላቸው ካማላ ሃሪስን ዕጩ አድርገው ካቀረቡ በኋላ ንግግር ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው ነው።

"አሜሪካውያን ወገኖቼ" በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ባይደን ፣ ንግግር በሚያደርጉበት ኦቫል ጽሕፈት ቤት፣ በታላላቆቹ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ፎቶ ግራፍ ተከበው ንግግር በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

"ሀገራችን የምትመራባቸውን ኗሪ ቃላት የጻፉት ቶማስ ጄፈርሰን፣ ፕሬዝደንቶች ነገሥታት እንዳልሆኑ ያስተማሩን ጆርጅ ዋሽንግተን፣ ክፉ መሥራትን እምቢኝ እንድንል የተማጸኑን አብራሃም ሊንከን፣ በፍርሃት እንዳንበገር ያበረታቱን ፍራንክሊን ሩዘቬልት" በማለት የቀደሙትን የዩናይድት ስቴትስ ፕሬዝደንቶች አስታውሰዋል።

"ይኽንን ታላቅ ጽሕፈት ቤት አከብረዋለኹ። ከዛ የበለጠ ግን ሀገሬን እወደዋለኹ" ብለዋል።

በአሜሪካ ፖለቲካ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ፕሬዝደንቱ ከኋይት ሐውስ "ኦቫል ኦፊስ" ጽሕፈት ቤታቸው ዛሬ ንግግር ሲያደርጉ።

ባይደን ከውድድሩ ለመውጣት የወሰኑት በሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሊሸነፉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ስጋቶች እየተበራከቱ በመሄዳቸው ነው።

ባይደን ቢሸነፉ፣ ሌሎቹንም ዲሞክራቶች አብረው ለሽንፈት ሊዳርጉ እንደሚችሉ የጠቆሙ የሕዝብ አስተያየት ግምገማዎችን ተከትሎ ለበርካታ ቀናት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጭንቀት ሲያወጡ ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ነው።

"አሜሪካን ታላቅ ሀገር የሚያደርጋት በነገሥታት እና በአምባ ገነኖች የማትገዛ ስለሆነች ነው" ያሉት ባይደን፣ "የሚያስተዳድራት ሕዝቧ ነው። ታሪክ በናንተ እጅ ነው፣ ሥልጣን በእናንተ እጅ ነው፣ የአሜሪካ እምነቷ ያለው በእናንተ እጅ ነው" ብለዋል።

ፕሬዝደንት ባይደን ከፕሬዝደንታዊ ምርጫው ዕጩ ተፎካካሪነት ለመውጣት መወሰናቸውን ባለፈው እሁድ በማኅበራዊ መገናኛ ካስታወቁ ወዲህ ዛሬ ለሕዝቡ ያደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ነው።

ባይደን በፕሬዝደንትነት በሚቆዩባቸው በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ትኩረታቸው ሥራቸውን ማከናወን እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ለዲሞክራሲ መቆም ከማናቸውም የሥልጣን ስም ይልቃል። የእኔ ብርታት እና ደስታ ምንጭ የአሜሪካን ሕዝብ ማገልገል ነው። ይሁን እንጂ አንድነታችን ምሉእ ይሆንልን ዘንድ የምናደርገው የተቀደሰ ጥረታችን የእኔ የግል ጉዳይ ሳይሆን የእናንተ የቤተሰቦቻችሁ የወደፊት እጣ ፈንታችሁ ነው። ያሉት ባይደን "የሀገራችን ዲሞክራሲ በመራጮቿ እጅ ነው " ብለዋል ጆ ባይደን

በፕሬዝደንትነት የሥልጣን ዘመናቸው ያከናወኗቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰጡት አመራር፣ ለሀገራቸው ያላቸው ራዕይ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የሚያበቃቸው መኾኑን የተናገሩት ባይደን ፣ ነገር ግን የፓርቲያቸውን አንድነት መምረጥ ስላለባቸው ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ባይደን ከሪፐብሊካን ፓርቲው ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትረምፕ ጋር ባደረጉት ክርክር ድክመት ያሳዩበት አፈጻጸም በአእምሮአዊ ብቃታቸው ዙሪያ ጥያቄ ካስከተለ በኋላ ከውድድሩ እንዲወጡ ውትወታው በርትቶባቸው ነበር ። ከእጩ ተፎካካሪነቱ ራሳቸውን ለማግለል ከወሰኑ በኋላ ግን ዲሞክራቶች ከጎናቸው በመቆም በፕሬዚደንትነት ስለአስመዘገቧቸው ክንዋኔዎች እንዲሁም ስለግል ባህሪአቸው አክብሮታቸውን ሲገልጹላቸው ይሰማሉ ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር፣ በ1972 ዓም በ29 ዓመታቸው ለዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተመርጠው የፖለቲካ ሞያቸውን የጀመሩት ባይደን፣ እንደ እ.አ.አ ጥር 20 ቀን 2025 ዓ.ም. በ82 ዓመታቸው ከሁሉም የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች የዕድሜ ባለጸጋው ፕሬዝደንት ኾነው የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቅቃሉ።

ፕሬዝደንት ባይደን በቀሪው የፕሬዝደንትነታቸው የመንፈቅ ጊዜ ሥራቸውን በትኩረት እያከናወኑ እንደሚቆዩ ያስታወቁ ሲሆን ነገ ሐሙስ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋራ ተገናኝተው ስለጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥረቶች ይወያያሉ ።

/ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል/