አየር መንገዱ ይህን ያስታወቀው፣ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን፣ ወደ አስመራ የሚደረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች፣ ከመጪው መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንዲያቋረጡ መወሰኑን ተከትሎ ነው፡፡
የአገሪቱ ሲቪል አቭዬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለሚጠቀሙ የኤርትራ መንገደኞች፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአገሪቱ ጋዜጣ ላይ አውጥቶታል በተባለና በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ሲዘዋወር በዋለ ማስታወቂያ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች እንደሚቋረጡ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ የእገዳ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ፣ በማኅበራዊ የትስስር ድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን፣ ከሦስት ቀናት በፊት፣ ባለፈው እሑድ፣ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ይህን ውሳኔ በደብዳቤ እንደገለጸለት ጠቅሷል፡፡
የአየር መንገዱ፣ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሐና አጥናፉ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ “የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን ከሁለት ሳምንት በፊት፣ የበረራ ቁጥሩን እንድናሳድግ በደብዳቤ አሳውቆን ነበር፤ አሁን ደግሞ በረራውን ሙሉ በሙሉ እንድናቋርጥ ሲነገረን ደንግጠናል፤” ብለዋል፡፡ የውሳኔውን ምክንያቶች በተመለከተም፣ ከሚመለከታቸው የኤርትራ ኃላፊዎች ጋራ እየተነጋገሩ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን አውጥቶታል በተባለው ማስታወቂያ እና ማሳሰቢያ፣ ለበረራዎቹ መታገድ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል፡፡ ከእነዚህ አንዱም፣ አየር መንገዱ “ተገቢነት የሌላቸው የንግድ ተግባራትን በመከተሉ ነው፤” ብሏል፡፡ በተጓዦች ላይ ምክንያታዊ ያልኾነ የበረራ ቲኬት ዋጋ ይጨመራል፤ ስልታዊ እና የተደራጀ የሻንጣ ስርቆትም ይፈጸማል፤ ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ይከሳል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች፣ ተደጋጋሚ የበረራዎች እና የሻንጣዎች መዘግየት እንደሚስተዋልም በማሳሰቢያው አመልክቷል፡፡
አቭዬሽኑ፣ እነዚህን እንደ መነሻ ከጠቀሰ በኋላም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ “ለችግሮቹ ካሳ አልሰጠም፤” በማለት ይወቅሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሮቹን እንዲያስተካክል የተሰጡ ማሳሰቢያዎችም ውጤት ባለማምጣታቸው፣ እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱንም፣ የሲቪል አቭዬሽኑ ማሳሰቢያ ያስረዳል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት፣ የአየር መንገዱ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሐና አጥናፉ በበኩላቸው፣ ለአየር መንገዱ በደረሰው ደብዳቤ ላይ፣ የእገዳው ምክንያቶች እንዳልተገለጹ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊዋ አክለው፣ የዛሬው የአቭዬሽኑ ማስታወቂያ ይዘት፣ “ከሁለት ሳምንት በፊት በኤርትራው ሲቪል አቭዬሽን ከተላከልን ሌላ ደብዳቤ ጋራ ይቃረናል፤” ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የበረራ ቁጥሩን እንዲያሳድግ በዚያው በሲቪል አቭዬሽኑ ደብዳቤ ተጠይቆ እንደነበር ኃላፊዋ አውስተው፣ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌላ ውሳኔ መተላለፉ አስደንጋጭ ነው፤” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ፣ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ በረራ መልሶ የተጀመረው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወር በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡