ከ400 በላይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት ቤቶች በግጭት ክፉኛ መጎዳታቸው ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

“እንደ ወታደራዊ ካምፕ ማገልገላቸው ማኅበራዊ ቀውስ አስከትሏል” - መምህራንና ወላጆ

በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ በዘንድሮውም ዓመት በቀጠለው ግጭት፣ ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የትምህርት መምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በተቀሰቀሰው ግጭት ዘንድሮም በመቀጠሉ፣ “ከ500 በላይ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ሳይሰጡ ከርመዋል፤” ብለዋል።

በዚኽም የተነሣ በተገባደደው የትምህርት ዓመት፣ ከ600ሺሕ በላይ ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ኃላፊው ገልጸው፣ በመጪው ዓመት ትምህርታቸውን ለማስጀመር ከኅብረተሰቡ ጋራ የዘመቻ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ተማሪዎች እና መምህራን፣ በዘንድሮው ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ልጆች “ለማኅበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤” ብለዋል፡፡