ዋሽንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ ከሪፐብሊካን ፕሬዝደንታዊ ዕጩና ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋራ ያደረጉትን ክርክር ተከትሎ በዕድሜያቸው ምክኒያት ስጋቶች መንፀባርቅ ከጀመሩ በኋላ፤ ራሳቸውን በድጋሚ ለመመረጥ ከገቡበት ፉክክር ራሳቸውን ማግለላቸውን ዛሬ አስታወቁ።
ባይደን ምርጫው አራት ወራት ሲቀሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 27 ከዶናልድ ትራምፕ ጋራ ያደረጉትን ክርክር ተከትሎ፣ በድጋሚ ለመመረጥ ከገቡበት ፍክክር እንዲወጡ እና ከዕጩነቱ ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚጠይቁ ዴሞክራቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
የ81 ዓመቱ ባይደን በክርክሩ ወቅት ትርጉም አልባ ምላሾችን በመስጠት እና ተፎካካሪያቸውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚገባ አልሞገቱም በሚል፣ ከዕጩነታቸው ግፊት ሲደረግባቸው ሰንብቷል።
የፕሬዝደንት ባይደን የሥልጣን ዘመን በመጪው በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ጥር 20 ቀን 2025 ዓ.ም ቀን ላይ ያበቃል።