የሃገሪቱን ሕግ ጥሷል በሚል ናይጄሪያ የፌስቡክ እና የዋትስአፕ ባለቤት በሆነው ሜታ ኩባንያ ላይ የ220 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት አስተላልፋለች። የፌዴራሉ የንግድ ፉክክር እና የተገልጋዮች መብት ጠባቂ ኮሚሽን ትላንት ዓርብ ባሳለፈው ውሳኔ፣ ሜታ የሃገሪቱን የመረጃ ጥበቃ እና የተጠቃሚዎች መብት ሕግጋትን በፌስቡክ እና በዋትስአፕ በተደጋጋሚ ጥሷል ብሏል።
የተገልጋዮች መብት ኮሚሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዳሙ አብዱላሂ መሥሪያ ቤታቸው ከናይጄሪያ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን ጋራ በመተባበር ከእ.አ.አ ግንቦት 2021 እስከ ታህሳስ 2023 ድረስ ባደረገው ምርመራ፣ ሜታ ኩባንያ በናይጄሪያ የተገልጋዮችን መረጃ ካለአግባብ መጠቀሙን ደርሰንበታል ብለዋል።
ሜታ ገበያ ካለ አግባብ በመቆጣጠር፣ የናይጄሪያውያንን የግል መረጃ ካለፈቃድ ለሌላ በማስተላለፍ እንዲሁም ናይጄሪያውያን የግል መረጃቸው በምን መልኩ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ራሳቸው እንዲወስኑ ባለመፍቀድ ጥፋተኛ መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
ሜታ ቅጣቱን ከመክፈል በተጨማሪ፣ የሃገሪቱን ሕግ እንዲያከብር እና ገበያውን እና የደንበኞቹን መረጃ ካለ አግባብ ከመጠቀም እንዲታቀብ ተጠይቋል።