የ10ሺሕ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የውጭ ጉዞ እገዳ መነሣቱን አገልግሎቱ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

ባለፉት 30 ዓመታት፣ ከደኅንነት እና ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ፣ የውጭ ጉዞ እገዳ የተላለፈባቸው 10ሺሕ ኢትዮጵያውያን ዜጎች፣ በዚኽ ዓመት ከእገዳ ነጻ መደረጋቸውን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዲሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ፡፡

የተቋሙ ኃላፊዎች፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ፣ ዛሬ ዐርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በበጀት ዓመቱ በስፋት የተስተዋለውን ፓስፖርት የማግኘት ችግርን ለማቃለል፣ 1ነጥብ1 ሚሊዮን ፓስፖርት ለማተም መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዓመቱ፣ በኢትዮጵያ፣ “በሕገ ወጥ ሰነድ ሲኖሩ ተገኝተዋል” በተባሉ 18ሺሕ የውጭ ዜጎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱንና ከእነርሱም ስድስት ሺሕዎቹ ከሀገር እንዲባረሩ መደረጋቸውን ኃላፊዎቹ ጠቅሰዋል፡፡