በምዕራብ ጎንደር ዞን በቀጠለው እገታ እና ግድያ ከባድ ስጋት ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ እና አካባቢው በታጣቂዎች በቀጠለው ግድያ እና እገታ የተነሳ ወጥቶ ለመግባት መቸገራቸውን እና ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎች ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ከጎንደር ወደ መተማ በሚወስደው መንገድ ልዩ ስሙ "መቃ" በተባለ ሥፍራ፣ ታጣቂዎች በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ባደረሱት ጥቃት፣ ሾፌሩን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ 14 ሰዎች ታግተው ወደ ጫካ እንደተወሰዱ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ፣ ከዞኑም ኾነ ከወረዳው ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች፣ በተለይ ለማስለቀቂያ ቤዛ ገንዘብ ሲባል የሚፈጸሙ ሲቪል ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ እገታዎች አሳሳቢ መኾናቸውን ጠቅሶ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ባወጣው የ2016 ዓ.ም. ሦስተኛ ዓመታዊ ሪፖርቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።